የመጪው ክረምት ችግኝ ተከላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ላይ ትኩረት ይደረጋል

157

ደሴ ግንቦት 9/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ በመጪው ክረምት ለሚተከሉ ችግኖች እየተደረገ ያለው ዝግጅት ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚሰጡት ላይ ትኩረት ማድረጉን የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን አስታወቁ፡፡

የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን ከሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የአማራ ክልል አመራሮች ጋር በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ለተከላ እየተዘጋጀ ያለ የቆላ ፍራፍሬ ችግኝን ተመልክተዋል፡፡

ሚንስትሩ ዑመር ሁሴን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደ ሀገር በመጪው ክረምት በአጠቃላይ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው።

በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ችግኞች ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በክልሎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ እቅዱን ለማሳከት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለተከላ እየተዘጋጁ ያሉ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬዎች የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ ሁሉም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲረባረብ አሳስበዋል።

በምስራቅ አማራ ቀጠና ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀምና አርሶ አደሩን በተግባር ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት በመስራት የታየው መልካም ጅማሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንዳሉት በክልሉ 18 ሚሊዮን የሚሆን ቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ችግኞቹን በ19 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል የተቀናጀ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለተከላ እየተዘጋጁ ካሉት ችግኞች ውስጥ 10 ሚሊዮን የቡና፣ 7 ሚሊዮን የቆላ ፍራፍሬ ተክሎች ሲሆኑ  ቀሪው የደጋ ፍራፍሬ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክልውም ከቡና ቀጥሎ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝና አፕል ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም አብራርተዋል።

እየተዘጋጁ ያሉት የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች በአርሶ አደሮች ማሳ፣ በባለሃብቶች በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እና በሌሎችም አካባቢዎች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ በበኩላቸው በዞኑ 7 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን የተመራው የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ትናንት ማምሻውን በቃሉ ሀርቡ የቆላ ፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያ ቡናን ጨምሮ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

በመስክ ጉብኝቱ የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።