የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የሴቶችን ይበልጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን ተዘጋጅቷል

90

ግንቦት 08/2014(ኢዜአ) የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የሴቶችን ይበልጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን መዘጋጀቱን ገለፀ።

በሊጉ ስራ አስፈፃሚ ውይይት ተደርጎባቸው በቀረቡ የግምገማ ውጤቶችና የውሳኔ ሃሳቦች ላይ ማእከላዊ ኮሚቴ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው አንደኛ ጉባዔ ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ከሊጉ አባላት ጋር በየደረጃው የተደረገው ውይይት አፈፃፀም ተገምግሟል፡፡

በተጨማሪም “ምግቤን ከጓሮዬ፤ ጤናዬን ከምግቤ” በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው የከተማ ግብርና ንቅናቄ የአፈፃፀም ደረጃና ሌሎች አጀንዳዎች ላይም መክሯል።

የሊጉ ፕሬዝዳንት መሰረት መስቀሌ፤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በፓርቲው ጉባኤ የተሰጡ ውሳኔዎችን አስመልክቶ በሁሉም ክልሎች ካሉ ሴቶች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።  

የከተማ ግብርና ስራዎች ሴቶች በስፋት እንዲተገብሩት ማድረግ በሊጉ በእቅድ ተይዞ ከፓርቲው ውይይት ጎን ለጎን በንቅናቄ የተከናወነ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሴቶች ያነሷቸው ጥያቄዎችም በህብረተሰቡ ከሚነሱና ከተለዩ ችግሮች ጋር ተቀራራቢ መሆናቸውን አንስተው የፓርቲው አቅጣጫ በሁሉም ደረጃ ተፈፃሚ እንዲሆን ሊጉ የሚጠበቅበትን ይሰራልም ብለዋል።

በከተማ ግብርና በመሰማራት የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ብሎም ጤናማ አመጋገብን ለመከተል በግብአት ጭምር ሴቶችን መደገፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የጓሮ አትክልትን በማልማት ሴቶች የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማነሳሳትን የማጠናከር ስራ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የሊጉን ፕሮግራም፣ ህገ-ደንብ እንዲሁም የአሰራርና አደረጃጀት መመሪያ ማሻሻያ ላይ ውይይት በማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው ማፅደቁንም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።

ከወራት በኋላ ለሚያካሂደው ጉባኤ የሚቀርበውን ሰነድ ማዕከላዊ ኮሚቴው አፅድቆ በሊጉ አባላት ለውይይት ቀርቦ እንደሚዳብርም ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ክረምቱ ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከልና የተተከሉትን የመንከባከብ ስራም ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል።    

የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የሴቶችን ተሳትፎና ይበልጥ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በሊጉ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን ተቀብሎ ለመፈፀምና ተግባራዊ ለማድረግ አባላቱ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንቷ አሳስበዋል።                 

የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች፣ የኑሮ ውድነትና የልማት ጥያቄዎች ሴቶች ባካሄዷቸው የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ መነሳታቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ በቅርቡ በሚያደርገው የመጀመሪያ ጉባዔ ሊጉ የሚጠቀምባቸው ፕሮግራሞች፣ ህገ-ደንብ፣ የአሰራርና አደረጃጀት መመሪያዎች ማሻሻያ እንዲሁም የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች፣ ተቋማዊ አሰራር ማሻሻል የውይይት አጀንዳዎች መሆናቸው ተገልጿል።

የሊጉ ማዕከላዊ ኮሚቴ በውይይት መድረኩ በቀጣይ ለሚያካሂደው ጉባኤ የሚቀርብ የሰነድ ዝግጅትና የፕሮግራምና ህገ-ደንብ ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አፅድቋል።