በመጪው ክረምት በአብዛኛው የሀገሪቷ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት ይኖራል

114

አዳማ፣ ግንቦት 08/2014(ኢዜአ) በመጪው ክረምት በአብዛኛው የሀገሪቷ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ ።

የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ግምገማ እና የመጪው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ የሚደረግበት መድረክ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።

ኢንስቲትዩቱ የመጪውን የክረምት ወቅት የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንበያን ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት የክረምት ወቅት የዝናብ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸው ስርጭቱን ጠንካራ ያደርገዋል ብለዋል።

በመሆኑም በመጪው ክረምት ስርጭት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቀዋል።

በተለይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቷ አካባቢዎች ላይ “በመጪው ክረምት የዝናብ እጥረት አይኖርም” ብለዋል።

ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት በሚኖራቸው አካባቢዎች ደግሞ ድንገተኛ ጎርፍ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል።

በዚህም የከፋ ጉዳት በሰውና በንብረት ላይ እንዳይደርስ ከወዲሁ የጎርፍ መከላከል ቅድመ ዝግጅትና የጥንቃቄ ስራ በመስራት ሊኖር የሚችለውን የዜጎች መፈናቀልና የንብረት መውደም ማስቀረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢንስቲትዩቱ የክረምት የአየር ሁኔታና የዝናብ ስርጭትን በተመለከተ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ጥራት ያለውን መረጃ ለህብረተሰቡና ለተጠቃሚው ባለድርሻ አካላት ለማድረስ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከደቡብ ምዕራብ የሚመጣው ዝናብ ወደ ሰሜን፣ ወደ ማዕከላዊውና ወደ ሰሜን ምስራቅ ዝናቡ ዘግይቶ ይገባል ያሉት አቶ ፈጠነ፤ በክረምት ወቅት የላሊና አየር ሁኔታ በመኖሩም ለክረምት ዝናብ መጠናከር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

ውስን የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ከመደበኛ በታች የክረምት ዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

በኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታ ትንበያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ በበኩላቸው ላሊና የአየር ፀባይ መኖሩ በክረምት ዝናብ መጨመር ላይ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም 85 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቷ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት የሚያገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከሰኔ  ወር ጀምሮ እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ድረስ የዝናብ አገባቡ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው ስርጭት እንደሚኖረው ይጠበቃልም ብለዋል።

በዚህም የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ በክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች አካባቢ ሊኖር የሚችለውን ጉዳትና አደጋ ለመቀነስ የተቀናጀ ዝግጅትና ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይ የተፋሰሶች ልማት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዘርፎች፣ ግብርናና ሌሎች ተቋማት የሚኖረውን የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስና ለመቋቋም በትኩረት መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ቅነሳ ላይ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

የፓሲፊክ ውቂያኖስ ከሚጠበቀው በላይ እየቀዘቀዘ በመሆኑ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንዲኖር አጋዥ የሆነው ላሊና የአየር ፀባይ እንደሚኖር ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል ።