የልፋቴ ክፍያ አትሌቶች ትልቅ ደረጃ መድረሳቸውና ሀገራቸውን በዓለም መድረክ ማስጠራታቸው ነው - አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን  የምትገኘው የበቆጂ ከተማ ዓለም አቀፍ ዝናን የተላበሱና ሀገራቸውን በአለም አደባባይ ያኮሩ በርካታ አትሌቶችን በማፍራት ትታወቃለች።

በቆጂ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚታወሰው የኢትዮጵያ ኩራት የሆኑና ስሟን ከፍ አድርገው ያስጠሩ አትሌቶችን ያፈራች መሆኗ ነው።

በቆጂ ካፈራቻቸው በርካታ አትሌቶች መካከል በ10 ሺ ሜትር የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ እህትማማቾቹ እጅጋየሁ፣ ጥሩነሽና ገንዘቤ ዲባባ፤ ወንድማማቾቹ ታሪኩና ቀነኒሳ በቀለ ይጠቀሳሉ፡፡

ለእነዚህ ጀግና አትሌቶች ስኬታማነት ከፍተኛ ድርሻ ካበረከቱ ሰዎች መካከል አሰልጣኝ ስንታየሁ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ስማቸው ይነሳል፡፡

በአለም አደባባይ ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚጠራው የበቆጂ አትሌቶች መካከል አብዛኞቹ በእሳቸው ስልጠና ስር ያለፉ መሆናቸው አይዘነጋም።

አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ በስራቸው፣ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ  ስፖርት እንቅስቃሴና ያፈሯቸውን አትሌቶች በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኢዜአ - አሰልጣኝ ስንታየሁ ዋና ስራዎ  የነበረው መምህርነት ነው፤ የአትሌቲክስ ስልጠናና መምህርነትን እንዴት ነበር አጣጥመው መጓዝ የቻሉት?

አሰልጣኝ ስንታየሁ - እውነት ነው ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ 25 ዓመት በስፖርት መምህርት ነበር ያገለገልሁት፤ ከዚያ በኋላም የወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ውስጥ ሰርቼአለሁ፤ እንግዲህ ከሙያዬ ጎን ለጎን ነበር ስልጠና የምሰጠው። ፍላጎቱ ካለ ምንም የሚያቆምህ የለም፤ ከስራ በፊትና ከስራ በኋላ ያለምንም እረፍት ነበር የምሰራው። በዚህ መልኩ ጡረታ እስከወጣሁበት ድረስ አገልግያለሁ። ከጡረታ በኋላ እስካሁንም ድረስ በበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በአሰልጣኝነት ተቀጥሬ እየሰራሁ እገኛለሁ።

ኢዜአ - ጡረታ የወጡት የጡረታ ጊዜዋ ደርሶ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አሰልጣኝ ስንታየሁ - የተወሰነ ዓመት እየቀረኝ ነው ጡረታ የወጣሁት አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ስለነበሩ በፍቃዴ ነው ጡረታ የወጣሁት።

ኢዜአ- የአትሌቲክስ ስልጠና በመስጠት ከሰላሳ ዓመት በላይ ሰርተዋል፤ እንዴት ነበር ልጆቹን የሚመለምሉት?

አሰልጣኝ ስንታየሁ - በወቅቱ ዝም ብዬ በፍላጎታቸው እንዲሮጡ አደርግ ነበር፤ ከዚያ አቅማቸውና ፍላጎታቸው የተሻለ በሆኑት ላይ አተኩራለሁ። አነርሱም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ለአትሌቲክሱ ትኩረት እንዲሰጡ አደርጋለሁ። በነገራችን ላይ በእኔ በኩል ያለፉ አትሌቶች በሙሉ መጀመሪያ ስልጠና ሲጀምሩ የነበራቸውን እድሜ፣ ቁመትና መሰል ጉዳዮች የሚያሳይ መረጃ እኔ ጋር  በዶክመንት ተቀምጦ ይገኛል።

ኢዜአ -እንደሚታወቀው  በግል ስልጠና የሚሰጡ አሰልጣኞች በክፍያ ነው ስልጠና የሚሰጡት እርስዎ ለሚሰጡት ስልጠና ክፍያ ይጠይቁ ነበር?

አሰልጣኝ ስንታሁ - ወደ 37 ዓመት አካባቢ ለሚሆን ጊዜ ስልጠና ስሰጥ ነበር፤ ከማሰለጥናቸው አትሌቶች ምንም አይነት ሳንቲም አልቀበልም፤ በነጻ ነው ስልጠናውን የምሰጠው። የእኔ ደሞዜም ክፍያዬም በዓለም መድረክ ኢትዮጵያን ማኩራታቸውና ትልቅ ደረጃ መድረሳቸው ነው።

ኢዜአ - በነጻ ስልጠና ሲሰጡአቸው ከነበሩት አትሌቶች ውስጥ በርካቶቹ ሀገራቸውን ከማኩራት ባለፈ  በግላቸው በገንዘብ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እነዚህ አትሌቶች የት እንዳሉ አስታውሰው ጠይቀዎት ያውቃሉ?

አሰልጣኝ ስንታየሁ - ብዙ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች እዚህ ሲመጡ በቃለ መጠይቃቸው የሚያነሱትን ጥያቄ ነው ያነሳሃው ፣ግን ማንም ዞር ብሎ የሚጠይቅ አትሌት የለም። አንዳንዶች በተወሰነ ጊዜ ወደ አካባቢው ሲመጡ እንኳን ሳይጠይቁኝ ነው የሚመለሱት። ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ለአትሌቶች በነፃ አገልግሎት የሰጠሁ ቢሆንም ለዚህ አበርክቶዬ በ2010 ዓ.ም 2ኛው የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ተብዬ ከመሸለሜ ውጭ እውቅና እንኳን አግኝቼ አላውቅም።

ኢዜአ - የአትሌቲክስ ስልጠና ብርድና ጸሀይን ችሎ መስራት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃልና በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፈው በሙያው እንዲቆዩ ያደረግዎት ምንድን ነው?

አሰልጠኝ ስንታየሁ- ሙያውን እወደዋለሁ፤ ቅድም እንዳልኩህ አትሌቶች ትልቅ ደረጃ መድረሳቸው ያስደስተኛል።

ኢዜአ - ክልሉስ ይህንን ልፋትዎን በመመልከት ለመደገፍና ለማበረታታት ያከናወነው ጥረት አለ?

አሰልጣኝ ስንታየሁ - በ2010 ዓ.ም 2ኛው የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚ በሚል እውቅና ተሰጥቶኛል፤ ከዚያ ውጭ አንድም ጊዜ በክልል ደረጃም ሆነ በዞን ወይም በከተማ ደረጃ እውቅናም ማበረታቻም አግኝቼ አላውቅም እሱ ቅር የምሰኝበት ነው። በዋናነት እንደዚህ አይነት እውቅናና ማበረታቻዎች ለሌሎች መነሳሳት በመፍጠር ከጊዜያዊ ጥቅም ይልቅ ህዝብና ሀገር የሚያስቀድም ትውልድ ለማፍራት ትልቅ ድርሻ አላቸው፤ ስለዚህ ረጅም ዓመት ያገለገልኩበት ክልል እውቅና ስላልሰጠኝ ቅር ተሰኝቻለሁ፤ ለሀገርና ለትውልድ ጊዜውን ሰውቶ የሚሰራን ሰው የማመስገን ልምዱ ማደግ አለበት።

ኢዜአ - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍና ዝቅ የማለት ነገር ይታይበታል፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጤታማነቱ እየቀነሰ ለመምጣቱ በቅርቡ በኦሊምፒክ የተመዘገበውን ውጤት በማሳያነት የሚጠቅሱ አሉ፤   ችግሩ የት ጋር ነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው ይላሉ?  

አሰልጠኝ ስንታየሁ - አሁንም የሀገሪቱ አትሌቲክስ ትልቅ ተስፋ የሆኑ አትሌቶች አሉ፤ ልዩነቱ በፊት ላይ አትሌቶች አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ፣ አታድርጉ ከተባሉም አያደርጉም። ዓላማቸውና ጽናታቸው  አስገራሚ ነበር። ውጤት በአቋራጭ መፈለግ አልነበረም፤ ሁሉም በጊዜው ይሆናል የሚል አቋም ነበራቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አትሌቶች ትዕግስት ሲያጡ ይታያል፤ የዓላማ ጽናታቸው እንደበፊቱ አይደለም፤ ቶሎ ውጤት መፈለግ ይታያል። ክለቦችና የአትሌቲክሱ ባለድርሻ አካላትም ያልተወጧቸው ብዙ የቤት ስራዎች አሉ። እነዚህን ማረምና የቤት ስራዎቹን መስራት ከተቻለ ከፍ ዝቅ የሚለውን ውጤት ማስተካከል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ኢዜአ - ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

አሰልጣኝ ስንታየሁ -እኔም ላደረጋችሁልኝ ቃለ መጠይቅ ከልብ አመሰግናለሁ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም