በመዲናዋ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ የቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

168

ግንቦት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የኅብረተሰቡን መሰረታዊ የቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚቀጥሉት አጭር ጊዜያት ተሰርተው ለኅዝብ የሚተላለፉ የልማት ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስጀምረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ 200 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገነባ ሲሆን ግንባታ በ1ሺህ 256 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል ተብሏል።

ቤቶቹ ባለ አንድ፣ ባለሁለትና ባለ ሦስት መኝታ ቤት ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን በአንድ ወለል ላይ አምስት ቤቶች ይኖሩታልም ነው የተባለው።

እያንዳንዳቸው 50 ቤቶች ያሏቸው አራት ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንጻዎች የሚገነቡ ሲሆን 50ዎቹ ቤቶች በመጪው ሦስት ወራት ይጠናቀቃሉ ተብሏል።

ቀሪዎቹ 150 ቤቶች ደግሞ በተመሳሳይ በፍጥነት ተጠናቀው በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የኅብረተሰብ  ክፍሎች እንደሚተላለፉም ተጠቁሟል።

ግንባታው በ82 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው ይኸው ግንባታ በከተማ አስተዳደሩና በባለኃብቶች የሚሸፈን ሲሆን ግንባታው ኦቪድ በተሰኘ ኩባንያ ይከናወናል ተብሏል።      

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታውን ባስጀመሩበት ጊዜ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የኅብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግርን ማቃለል ዋነኛ አጀንዳው ነው።

በቀጣይ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት ኪራይ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።  

በዛሬው ዕለት ግንባታቸው የተጀመሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በቅርቡ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍ ነው ያረጋገጡት።  

የክፍለ ከተማው አመራሮች የተጀመረው ሥራ እውን እንዲሆን የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

ኅብረተሰቡም የሚሰሩ መሰረተ ልማቶችን በእኔነት ስሜት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበው ግንባታውን ለሚያግዙ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በበኩላቸው ከጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ጎን ለጎን በቀጣይ ለ300 አቅመ ደካማ ነዋሪዎች የቤት እድሳት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማው 1ሺህ 500 ለሚሆኑ ወገኖች የሚመገቡበት ሁለት የምገባ ማዕከላት እንዲሁም  32 የሸገር ዳቦ ማቅረቢያ ቦታዎችን የማዘመን ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በክፍለ ከተማው በሚገኙ በእያንዳንዱ ወረዳዎች አንድ አንድ የዳቦ ፋብሪካዎች ለመገንባት መታቀዱን ጠቁመው በዛሬው ዕለት አራቱ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም