በጋምቤላ ለኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እየተሰጠ ነው

90

ጋምቤላ፤ ግንቦት 8/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች ከ241 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝና የፕሮጀክት ፋይናንስ ብድር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

ባንኩ ከ400 ለሚበልጡ መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በጋምቤላ ከተማ ሰጥቷል።

የጋምቤላ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ አያል ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ባንኩ በጋምቤላ ክልል የአነስተኛና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍ እያደረገ ነው።

ቀደም ሲል በክልሉ በፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር አገልግሎት የነበሩ የአሰራር ክፍቶችን የማስተካከል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ለኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች ከ241 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝና የፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ለክልሉ በዚህ ዓመት ለሊዝና ለፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ከተመደበው በጀት ለስምንት ኢንተርፕራይዞች ከ42 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ቀሪውን ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ባንኩ የሚጠየቀውን መስፈርት አሟልተው ለሚቀርቡ ደንበኞች የሊዝና የፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘርፉ በክህሎትና በቴክኖሎጅ ተደግፎ ውጤታማ እንዲሆን በባንኩ በኩል የስልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጋምቤላ ከተማ  ሰሞኑን ከ400 በላይ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና ባለሃበቶች የተሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በማሳያነት አንስተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ቤል ኬት የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሽ  በበኩላቸው በስልጠናው በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስፈልጉ መስፈርቶችና መመሪያዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አግኝቻለሁ ብለዋል።

በተጨማሪም በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል።

ሌላው የስልጠና ተሳታፊ አቶ ሙሃባ መኮንንም የሚያከናወኗቸው የልማት ስራዎች፣ የፋይናንስ አጠቃቀምና አስተዳደር በእቅድ ለመምራት የሚያስችል ግንዛቤ በስልጠናው ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም