በዕውቀት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ኢዜአ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል

92

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዕውቀት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ከሰራተኞቹ እና ከባለድርሻ አካላት ያሰባሰባቸውን ከ5 ሺህ በላይ የተለያዩ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበርክቷል፡፡

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ኢዜአ በዋናው እና በቅርንጫፎቹ ከሚገኙ ሰራተኞቹና በተቋሙ ከነበሩ የቆዩ መጻሕፍትን በማሰባሰብ በመጀመሪያ ዙር ያበረከተው የመጻሕፍት ልገሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

አዲሱ ትውልድ በአገር ግንባታ ሂደት የራሱን አሻራ ያሳርፍ ዘንድ በንባብ መታነጽ እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህ የሚያግዙ መጻሕፍትን ተደራሽ ማድረግ የሁሉም ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቀጣይም በዕውቀት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ በንባብ የታነጸ ግለሰብ፣ ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ለአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና አገራትም የተገነቡት በዕውቀት በዳበሩ ዜጎች እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዕውቀት የዳበረ ትውልድ እንዲፈጠር በመሻት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ላደረገው የመፅሓፍት ልገሳም ምስጋና ችረዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትና ለኢዜአ መጽሐፍትን የለገሱት ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ፤ የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት መገንባት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ትልቁ ቁም ነገር መጻሕፍት ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ለአንባቢያን ተደራሽ በማድረግ እንደ አገር አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር በየወረዳው አብያተ መጻሕፍትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ የገባ ሲሆን የመጽሃፍት ማሰባሰብ ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍትን የመያዝ አቅም አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም