ኢትዮጵያ ያሏትን ቋንቋዎች በሥነ-ጽሁፍ በማዳበር አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይገባል

145

ግንቦት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ ያሏትን ቋንቋዎች በሥነ-ጽህፍ በማዳበርና ተደራሽነታቸውን በማስፋት አንባቢ ትውልድ መፍጠር ይገባል ሲል ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላት ተናገረ።

ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ በሥነ-ጽሁፍና በመምህርነት ሙያ አገሩን በማገልገል ላይ የሚገኝ ሥመ-ጥር የጥበብ ባለሙያ ነው።  

በዚህም ተወዳጅነትን ያተረፉ በጋሜ መቅረት፣ ሾተላይ፣ ድሃ አደግ፣ መንታ እናት፣ ከድጃና ሌሎች የታተሙና ለህትመት ዝግጅት የተሰናዱ በርካታ መጻህፍትን ደርሷል።

ከዚህ ጎን ለጎን  በስብዕና ግንባታ፣ በፖለቲካዊ፣ በምጣኔ ኃብት፣ በባህልና ሌሎች ጉዳዮች ይዘት ያላቸው ከ4 ሺህ እስከ 6 ሺህ የሚጠጉ መጻህፍት ባለቤትም ነው።

ከእነዚህም መጻህፍት መካከል የአብርሆት ቤተ-መጻህፍትን ለማደራጀት የሚውል በርካታ መጻህፍት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በኩል ድጋፍ አድርጓል።

የአብርሆት ቤተ-መጻህፍት የንባብ ማዕከልም ኢትዮጵያዊያን ለማንበብ የሚፈልጓቸውን የምርምና ሌሎች አይነት መጻህፍት በአንድ ቦታ ተሰባስበው እንዲገኙ ይረዳል ብሏል።   

በዘላቂነትም ኢትዮጵያ ያሏትን የቋንቋ ብዝኃነት ከፖለቲካ ፍጆታ ባለፈ በድርሰትና ሥነ-ጽሁፍ ዳብረው ተደራሽ ሚሆኑበትን አውድ መፍጠር እንደሚገባ መክሯል።

በሥነ-ጽሁፍ የዳበረ ቋንቋን በመፍጠርም የብዝኃ ልሳን ድርሰትና ትርጓሜ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግሯል።

የአገር ውስጥ ቋንቋ ትርጓሜ ማዕከልን በማቋቋም የቋንቋ ትስስርና ተግባቦትን የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ትኩረት እንደሚሻ ገልጿል።

የአገር ውስጥ ቋንቋ ትርጉምና ልማት ማዕከልን በማቋቋም አንዱ የሌላውን የሚያይበትና የሚያውቅበትን መድረክም መፍጠር ይገባል ብሏል።

በኢትዮጵያ እየተፈጠረ የሚገኘው ጥላቻና አለመግባባትም አንዱ የአንዱ ምንነት የሚረዳበትን የንባብና ድርሰት ተደራሽነት ባለመሠራቱ እንደሆነ አንስቷል።

እንደ አብርሆት ያሉ የንባብ ቤተ-መጻህፍትም "የንባብ ልህቀት ማዕከል" ሆነው በማገልገል ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም መስፋት እንዳለበት አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም