በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው

86

ግንቦት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ።

የክልሉ የኢንቨስመንት ፎረም " ሃላፊነት የተላበሰ የግብርና ኢንቨስትመንት ለሁለንተናዊ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ነው ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢኖሩትም በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም ረገድ ውስንነቶች አሉ።

ለረጅም ዓመታት በነበረው ኢፍትሃዊ አሰራር ምክንያት የክልሉ ህዝብ እና መንግስት በሃብቱ ላይ የመወሰን ስልጣን መነፈጉ ነው ብለዋል።

ይህም የክልሉ ህዝብ የበይ ተመልካች በመሆን በድህነት እንዲቆይ እንዳደረገው አቶ አሻድሊ ጠቁመዋል።

በሰፊው ህዝብ የጋራ ጥረት በመጣው ለውጥ የክልሉ ህብረተሰብ በሃብቱ ላይ በባለቤትነት ከመወሰን በላይ አልምቶ ከድህነት የመውጣት ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ኪራይ ሰብሳቢነት እና ቢሮክራሲያዊ አሰራርን ጨምሮ የፀጥታ ችግር በዘርፉ እንቅፋት መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት የተቀናጀ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአርሶ አደሩ ተሞክሮ ከማካፈል ጀምሮ ግብር በአግባቡ በመክፈል የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ አሻድሊ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው በክልሉ ከ2012 ዓ.ም በኃላ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መሻሻሉን ጠቁመዋል።

የወሰዱትን መሬት በብድር አስይዘው በመሰወር መንግስትን ከፍተኛ የግብር ገቢ ያሳጡ የአንዳንድ ባለሃብቶችን ጉዳይ ሲጠቅሱ በዘርፉ አሁንም ማነቆዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

የኢንቨስትመንት ፎረሙ እስከ ግንቦት 09 / 2014 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን ከ300 በላይ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም