''ለፍቅር እሮጣለሁ'' በሚል በተካሄደው ሩጫ ላሸነፉ አትሌቶች ሽልማት ተሰጠ

125

ድሬደዋ፤ ግንቦት 7/2014 (ኢዜአ)፡ ''ለፍቅር እሮጣለሁ'' በሚል በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ላሸነፉ አትሌቶች ሽልማት ተሰጠ።

የድሬዳዋን አደባባዮችና ዋና ዋና ጎዳናዎች ባካለለው የሴቶች ውድድር በግል የተወዳደረችው አትሌት እመቤት ንጉሴ ከለገጣፎ አንደኛ ስትወጣ ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እና አዳኔ እንግዳው ከአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ክለብ ሁለተኛና ሶስተኛ በመውጣት  አሸንፈዋል፡፡

በወንዶቹ ምድብ በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ገመቹ ጊሼ ከፌደራል ፖሊስ፣ ደበበ ተካ ከፌደራል ማረሚያ  አንደኛና ሁለተኛ  ሆነው ሲያሸንፉ  አትሌት ሙሉጌታ አሰፋ ከመከላከያ ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል፡፡

ለአሸናፊዎቹ የወርቅ፣ የብርና የናሃስ መዳሊያ የተበረከተ ሲሆን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ የ50 ሺህ ፣ የ20 ሺህ ብር እና 15ሺህ ብር ሽልማት በቀደም ተከተል አግኝተዋል።

ከዚህም ባሻገር በሁለቱም ፆታዎች ውድድር እንደኛ ለወጡት አትሌቶች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

እንዲሁም በውድድሩ እስከ 10ኛ ደረጃ ላገኙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለውድድሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱት የሚዲያ ተቋማት፣ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

ሽልማቱን የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ ውድድሩን ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሂማሬስ ኢንተርናሽናል አመራር ኮማንደር ጌጤ ዋሚና የሀገሪቱን ዕውቅ አትሌቶች ያፈሩት ኮማንደር ሁሴን ሼቦ፣ የኢትዮጵያ ታዋቂ አትሌቶች ሰንበሬ ተፈሪ፣ ሻለቃ አሊ አብዶሽ ፣ የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ፍራኦል ቡልቻ፣ የድሬዳዋና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ለአሸናፊዎቹ ሽልማታቸውን ባበረከቱበት ወቅት እንዳሉት ስፖርት ፍቅር፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ እድገት፣ ጤንነት፣ አምራችነት፣ ንቃትን ለሁሉም ተልዕኮ ዝግጁነት በማጎናጸፍ በኩል ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ድሬዳዋ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻዎችና ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነት ለማሳወቅም አግዟል ብለዋል፡፡

የሂማሴስ ኢንተርናሽናል መሪ አትሌት ኮማንደር ጌጤ ዋሚ በበኩላ በድሬዳዋ የተዘጋጀው የጎዳና ውድድር ውጤታማ እንደነበር ተናግራለች።

ድሬዳዋ በአትሌቱም ዘርፍ ሀገር የሚያስጠሩ አትሌቶች ለማፍራት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም