በዞኑ ለጤና መድህን ተጠቃሚዎች መድሀኒት የሚያቀርቡ አራት የህዝብ መዳህኒት ቤቶች ተከፈቱ

127

ፍቼ ግንቦት 07/2014/ኢዜኣ/ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በጤና መድህን ለታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ መድሀኒት ለማቅረብ የሚስችሉ አራት የህዝብ መድሀኒት ቤቶች ተከፍተው ለአገልግት መዘጋጀታቸውን የዞኑ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት  ቤት ኃላፊ  አቶ አሰፋ መስፍን ዛሬ በፍቼ ከተማ ለአገልግሎት የተዘጋጁ መድሀኒት ቤቶችን  ሲመርቁ እንደገለጹት መድሀኒት ቤቶች በክልሉ መንግሥትና  በህዝብ መዋጮ  የተሰሩ  ናቸው።

መድሀኒት ቤቶቹ በዞኑ በፍቼ፤ በአለልቱ፤ በውጫሌና ጅዳ ከተሞች የውስጥ ቁሳቁስና መዳህኒት ተማልቶላቸው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል።

ለመድሀኒት ቤቶቹ  የክልሉ መንግስት ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን  ብር በላይ  ወጪ ማድረጉን ጠቁመው የከተሞቹ ነዋሪዎችም 400ሺህ ብር በማዋጣት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

መድሀኒት ቤቶቹ  በከተሞቹ በጤና መድህን ለታቀፉ 350ሺህ ህዝብ በስፋትና  በተመጣጣኝ ዋጋ  የመዳህኒት አቅርቦት የሚሰጡ መሆኑንተናግረዋል።

ከጤና ጋር ተያዥነት ያላቸው  የላብራቶሪና  የመመርመሪያ  መሳሪያዎች አገልግሎት የመስጠትዓላማ ያላቸው መሆኑንም አመልክተዋል ፡፡

የህዝብ መድሀኒት ቤቶች ለዓመታት በህዝብ ይከፈትልን ጥያቄ ሲጠየቁ  የነበሩ  መሆኑን  ግምት ውስጥ በማስገባት የክልሉ መንግስት የሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመድሀኒት ቤቶቹ ለስኳር፤ ለደም ግፊት፤ ለሳንባ ነቀርሳና ኩላሊት ህሙማን  አገልግሎት የሚውሉትን ጨምሮ መድሀኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ  የሚያቀርቡ  መሆኑንም አመልክተዋል።

የፍቼ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማሞ ታደሰ  በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለአገልግሎት የተዘጋጁ መድሀኒት ቤቶች  በህዝብ ፍላጎት የተቋቋሙ ናቸው፡፡

ይህም በአካባቢው  በጤና  ጣቢያዎችና  ሆስፒታሎች  የሚታዘዙ መድሀኒቶችን ለህዝቡ  በተመጣጣኝ ዋጋ  ለማቅረብ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመድሀኒት ቤቶቹ መከፈት በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች  በመድሀኒት ፍለጋ የሚባክኑትን ጊዜ፤ጉልበትና ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ መደሰታቸውን የተናገሩት የከተማው ቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ቸርነት አበራ ናቸው ፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ ነዋሪዎች፤ የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን ተጨማሪ መድሀኒት ቤቶችን ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን የዞኑ ጤና ጥበቃ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡