በሐረሪ ክልል የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል

105

ሐረሪ፤ ግንቦት 7/2014 (ኢዜአ)፡ በሐረሪ ክልል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀከቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች አመራሮች የተጠናቀቁ የጋራ መጸዳጃ ቤቶችንና  የንጹህ መጠጥ የውሃ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቶችን ዛሬ ስራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው።

ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ከማስገንባት አንጻር ክፍተት መኖሩን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች እንዲጠናከሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የክልሉ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን  እንዳሉት ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃና ሳኒቴሽን ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በክልሉ ከተገነቡት 17 የህዝብ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ስምንቱ ተጠናቀው ዛሬ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸው፤ የቀሪዎቹ ስራም ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የንጹህ መጠጥ ውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን በክልሉ የሚገኙ 409 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን  የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስት በህዝብ ውይይት ላይ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማቃለል ስራ እያከናወነ መሆኑን በክልሉ ሸምኮር ወረዳ ነዋሪ አቶ መስፍን ላቀው ገልጸዋል።

የልማት ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ ከህዝቡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ዋናው ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ አልማዝ ዓለሙ በበኩላቸው የልማት ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ ችግሮቹን መፍታት ማስቻላቸውን ገልጸዋል።