በቦቆጂ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ የታላቁ ሩጫ ውድድር አትሌት ደጀኔ ሃይሉና አትሌት መሰረት ሂርጳ አሸነፋ

147

ግንቦት 7/2014 (ኢዜአ)  በቦቆጂ ከተማ ለመጀመሪያ በተደረገ የታላቁ ሩጫ በ 7 ኪሎሜትር ውድድር በወንዶች አትሌት ደጀኔ ሃይሉ በሴቶች አትሌት መሰረት ሂርጳ አሸንፈዋል።

በዚህ መርሃ ግብር የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ  ሰላማዊት ዳዊት፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሰዓዳ ኡስማን ጨምሮ የተለያዩ  የዞንና የከተማ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ።

"ኢትዮጵያ ትሮጣለች" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውድድር በአዋቂዎች 7 ኪሎ ሜትር ሩጫ፣  15 ኪሎ ሜትር ብስክሌት ውድድርና የህጻናት ሩጫ ተካሂዷል ።

በአዋቂ ወንዶች የ7  ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ደጀኔ ሃይሉ  በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ አትሌት ቱሉ አበበ ሁለተኛ፣ አትሌት ብርሃኑ ቱሉ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ  ይዘው  አጠናቀዋል።

በሴቶች 7 ኪሎሜትር  ውድድር ደግሞ አትሌት መሰረት ሂርጳ በአንደኝነት አጠናቃለች።

ቀነኒ ዲቻ እና ሃዊ ጉደታ  እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ጨርሰዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት፣ የውድድሩ ዓላማ  የስፖርት ቱሪዝምን ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል።

በቆጂ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያስጠሩ ጀግኖችን ያፈራች ከተማ መሆኗን አስታውሰው ውድድሩ መካሄዱ ከተማዋን የበለጠ ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ መርሃ ግብሩ ቱሪዝምን ከማሳደግ በተጨማሪ ታዳጊ ስፖርተኞችን  የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል ።

ታላቁ ሩጫ  በቦቆጂ ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በየዓመቱ ለማካሄድ እንደታቀደም  ጠቁመዋል።

የቦቆጂ የስፖርት ቤተሰቦች ከተማዋ እንዳፈራቻቸው አትሌትና እንደ ስሟ በመሰረት ልማትና በልማት ተጠቃሚነቷ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ ።

እንደዚህ አይነት ሀገር አቀፍ ውድድሮች መቀጠል  እንዳለባቸውና ለከተማው ነዋሪና ኢኮኖሚ መነቃቃት  የቱሪዝም ተጠቃሚነትን ለማሳደግ  ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት ።

በቦቆጂ ታላቁ ሩጫ  በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች  የስፖርት ቤተሰቦች በቦታው ተገኝተው ውድድሩን ተከታትለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም