በወራቤ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትንና የንግድ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ገንዘብ እየተሰባሰበ ነው

86

ግንቦት 7/2014 (ኢዜአ) በወራቤና አካባቢው ጉዳት የደረሰባቸውን አብያተ ክርስቲያናትንና የንግድ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ኅብረተሰቡ ገንዘብ እያሰባሰበ መሆኑን የስልጤ ዞን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰውን ውድመት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙርሰል አማን እንዳሉት፡ የእምነት ተቋማቱን ገንብቶ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከህብረተሰቡ ጋር እየተሰራ ነው።

በወራቤና አካባቢው የተሞከረውን ግጭት ሕብረተሰቡ በአንድነት ሆኖ ማክሸፍ መቻሉንም ጨምረው ተናግረዋል።

እስካሁን የተለያዩ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ድርጊቱ የስልጤ ሕዝብ እሴት ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዳወገዘውም አቶ ሙርሰል አውስተዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ድርጊቱ ሃይማኖትን የማይወክል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተ-እምነቶች መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ርብርብ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፡ ሀይማኖታዊ አስተምህሮዎች ማዕከላቸው የሕዝብ አንድነት መሆን አለበት።

የሁሉም ቤተ-እምነት አባቶች በተቋማቸው ላይ የሚሰጡትን አስተምህሮዎችን መቆጣጠርና መከታተል እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

ሌላው በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ምክር ቤት አባል ሼህ መሀመድ ሲራጅም እንዲሁ በእስልምና እና ክርስትና መካከል ችግር ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አይሳካላቸውም ብለዋል።

መሰለ አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን መከላከልና ማስቆም እንደሚገባ ሼህ መሀመድ አሳስበዋል።  

በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመገንባት ለሌሎች አካባቢዎች ማስተማሪያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው።

ፓስተር ጻድቁ አያይዘውም በቀጣይ መሰል ችግሮች እንዳያጋጥሙ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባቶች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ-ክርስቲያን ዋና ፀሐፊ ዶክተር ስምዖን ሙላቱ በቤተ እምነቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች እንዳይደገሙ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት በመንግሥት አካላትና በሌሎች ቤተ -እምነቶች የተደረገው ድጋፍ ሊዳብር የሚገባ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ፣ በሳንኩራና ምሥራቅ አዘርነት ወረዳዎች በሰባት ቤተ-እምነቶች ላይ ጉዳትና ውድመት መድረሱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም