የዞኖቹ ነዋሪዎች ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት መስራት ይገባል-ዋና አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

147

እንጅባራ ፤ግንቦት 7/2014 (ኢዜአ) በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተዋሳኝ የሆኑ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የመተከል ዞኖች ነዋሪዎች ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር  እና የመተከል ዞን ነዋሪዎችን የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል የውይይት መድረክ ዛሬ በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በውይይቱ ላይ እንዳሉት የአማራና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ  በአንድነት፣ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ለዘመናት የኖረ ነው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማተራመስ እኩይ ዓላማ እንግበው በንጹሃን ዜጎች ላይ ግፍ ፈጽመዋል።

የሁለቱ ዞኖች ነዋሪዎች ለዘመናት የዘለቀውን የህዝብ ለህዝብ የቆየ ትስስር በዘላቂነት ማስቀጠልና ማጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ እንዳሉት የሁለቱ ዞኖችን  ነዋሪዎች ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት መስራት ይገባል።

የአማራ ክልል መንግሥት ለሁለቱ ዞኖች ነዋሪዎች መልካም ግንኙነት መጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ የውጭና የውስጥ ጠላቶች በሀሰት ትርክት የዞኖቹን ነዋሪዎች አንድነትና ትስስር ለመሸርሸር ሞክረዋል።

ለዘመናት አብሮ የኖረው የሁለቱ ዞኖች ነዋሪዎች የአብሮነትና የአንድነት እሴት ጠንካረ በመሆኑ ያሰቡት አልተሳካላቸውም ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ውይይት መድረኩ ዋና ዓላማ ችግሮችን በማረም የሁለቱን ዞን ነዋሪዎች እህትማማችነትና ወንድማማችነትን ማጠናከር ነው።

''የአጎራባች ዞኖች እንደመሆናችን የጋራ እሴቶቻችንን አጠናክረን ሰላማችንን የምናስጠብቅበትና የሴረኞችን አጀንዳ የምናከሽፍበት አሰራር ለመዘርጋት ውይይቱ አስፈላጊ ነው'' ብለዋል።

ይህም የአካበቢውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የስራ ዘርፎችን በማስፋፋት የሁለቱን ዞኖች ነዋሪዎች የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው ከውስጥና ከውጭ የገጠሙንን ፈተናዎች ለማሸነፍ ህዝባዊ አንድነታችን መጠናከር አለበት ብለዋል።

ለዚህም ለዘመናት የዘለቀውን የአብሮነት እሴታችንን በማስቀጠል የሁለቱ ዞኖችን ነዋሪዎች ሰላም በማረጋገጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋምና አካባቢውን ማልማት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂ ሰላም በማስፈን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በውይይቱ የአማራና ቤንሻንጉል ክልሎች ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ የዞኖቹ አስተዳዳሪዎች፣ የአጎራባች ወረዳዎች የህብረተሰቡ ተወካዮች፣ የእንጅባራና አሶሳ ዩኒቨርስቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም