በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከ37 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል

87

ነቀምቴ ግንቦት 06/2014 /ኢዜአ/በምሥራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ37 ሺህ ለሚበልጡ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ዓለምገና አዱላ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር  ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ37 ሺህ በላይ ወጣቶች  ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ወጣቶቹ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በማዕድን ማውጣት፣ በእንስሳት እርባታ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

ለወጣቶቹ 1ሺህ 457 ሄክታር መሬት እና 137 የማምረቻና የምርት መሸጫ ሼዶች እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

እንዲሁም ከ17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መመቻቸቱን  አቶ ዓለም አስረድተዋል።

እሳቸው እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 31 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለማስመለስ ተወጥኖ እስካሁን የዕቅዱን 80 በመቶ  ማሳካት ተችሏል።

በዞኑ የዲጋ ወረዳ የቀርሳ ዳኮ ወጣት ገመቹ አበራ በሰጠው አስተያየት ከሶስት ወራት በፊት 40 ሆነው ተደራጅተው በቆጠቡት 3ሺህ ብር የአሸዋ የማውጣት  ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸው 114ሺህ ብር መድረሱንና ለ10 ሰዎችም ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድቷል።

 ከአሸዋ ማውጣት በተጓዳኝ የግብርና ስራ ለመጀመር መዘጋጀታቸውም ወጣት ገመቹ ገልጿል፡፡

በዞኑ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የጅሬኛ ቀበሌው ወጣት በላይ ኢንኮሣ በበኩሉ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በማህበር ተደራጅተው አጠቃላይ የግንባታ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ተናግሯል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ አስተዳደር የአጥር ግንባታ ሥራ ለመፈጸም ተወዳድረው በማሸነፍ በ3 ሚሊዮን ብር ገንብተው ማጠናቀቃቸውንም አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም