የሙያ ብቃት ምዘናው ክፍተቶቻችንን ለመለየት ይረዳናል...የሃዋሳ ታቦር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን

122
ሃዋሳ ግንቦት 10/2010 የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ከትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ባለፈ መምህሩ ሙያዊ ክፍቶቹን በመለየት በተሻለ እንዲሰራ የሚያነሳሳው ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ታቦር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ገለጹ። በደቡብ ክልል ከ16 ሺህ በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ቅዳሜ የሚሰጠውን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምዘና ፈተና እንደሚወስዱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።፡፡ በትምህርት ቤቱ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት ተሾመ ሀሰና እንዳሉት ምዘናው መምህሩ ያለውን አቅምና ክፍተት ለይቶ ክፍተቱን በመሙላት ለተማሪዎቹ በቂ ዕውቀት ለማስጨበጥ የሚያግዝ ወሳኝ ነገር ነው። አንዳንድ መምህራን በፈተናው ብንወድቅ ከስራ ልንባረር እንችላለን በሚል ፍርሀት እንዳልተመዘገቡ ጠቁመው መምህር ሳያነብና ሳይዘጋጅ ለማስተማር እንደማይችል አውቀው በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ለመፈተን መፍራት እንደማይገባ ተናግረዋል። ላለፉት 12 ዓመታት በሂሳብ መምህርነት እንዳገለገሉ የተናገሩት መምህር አስጨናቂ ካሳዬ የሙያ ብቃት ምዘና ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት፣ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና የመምህሩን አቅም ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል። "አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎች በዚህ መምህር ከምንማር በራሳችን ጊዜ አጥንተን ብንፈተን ይሻላል" የሚሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ይህን ነገር ለማስቀረት የሙያ ፈቃድ መሰጠቱ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመምህራን ትምህርት አመራር ልማትና የሙያ ፈቃድ እድሳት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ፋንታዬ እንዳሉት የአመቱ የመምህራንና ርዕሰ መምህራን የሙያ ብቃት ምዘና ቅዳሜ ግንቦት 11 ይሰጣል፡፡ ፈተናውም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተዘጋጁ 31 ጣቢያዎች እንደሚሰጥና 16 ሺህ 55 መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ለመፈተን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል። በቢሮው የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማርቆሰ ቡልቻ እንዳሉት በክልሉ ከ120 ሺህ በላይ መምህራን የሚገኙ ሲሆን በክረምትና በርቀት በትምህርትና በስልጠና ላይ ያሉትን ሳይጨምር ለሙያ ብቃት ምዘና ብቁ የሆኑት 97 ሺህ ናቸው፡፡ መምህራን በተመረቁበትና በሚያስተምሩት ሙያ የሚመዘኑ በመሆኑ የሚከብድ ነገር እንደሌለው ገልጸው ከዝግጅት ማነስና ከምዘና መሳሪያዎች ብቃት ጋር በተያያዘ ጉድለት እንደነበረ ጠቁመዋል። ከዚህ ባለፈም የሙያ ብቃት ምዘናው በሃገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ ወጥ ሆኖ ባለመቀጠሉ መዘናጋት ፈጥሮ እንደነበረም አስረድተዋል። ከኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ወደ ሙያው አዲስ የሚቀላቀሉ መምህራን የጽሁፍ ፈተና ብቻ ሲወስዱ ነባርና ልምድ ያላቸው መምህራን ከጽሁፍ በተጨማሪ የተግባር ፈተና እንደሚሰጣቸው አቶ ማርቆስ አስታውቀዋል፡፡                                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም