የሶማሊያ ሕግ አውጭዎች ሽብርተኝነትን ለመከላከል ፖለቲካዊ ውይይት እንዲካሄድ አሳሰቡ

151

ግንቦት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሶማሊያ አዲስ የተመረጡ የፓርላማ አባላት በሃይል ለመቆጣጠር ያልተቻለውን ሽብርተኝነት ለመከላከል ከአማጽያን ጋር ፖለቲካዊ ውይይት እንዲካሄድ አሳስበዋል።

ተመራጮቹ በአገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሶማሊያ መንግስት ከአማጽያን ጋር በጠረጴዛ ዙርያ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ነው የጠየቁት።

ተመራጭ የፓርላማ አባል የሆኑት ሳዲቅ አብዱላህ አብዲ ለአናዶሉ በሰጡት አስተያየት “በሽብርተኝነት የተፈረጀውን አልሻባብን ጨምሮ ሌሎች አማጽያንን በኃይል ማጥፋት እስካልተቻለ ድረስ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ውይይት ማካሄድ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የአፍሪካ ሕብረት ብቻ ሳይሆን እንደ ቱርክ ያሉ ወዳጅ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፋቸውን ሊሰጡ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

ኦማር ኢብራሂም አሺ በበኩላቸው “ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ማጣትን የምትቋቋምበት ሁኔታ ላይ አይደለችም፣ ከወታዳራዊ እርምጃ ውጭ የሆኑ አማራጮችን መዳሰስ ይገባናል” ብለዋል።

ከአልሻባብ ጋርም በመወያየት በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስበትን ስትራቴጂ የመንደፊያው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ አመልክተዋል።

ለረጅም ጊዜያት የተራዘመው የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዛሬው ዕለት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም