በድሬዳዋ "ለፍቅር እሮጣለሁ" የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው

115

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በድሬደዋ በርካታ አላማዎች ያነገበ "ለፍቅር እሮጣለሁ" የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እየተካሄደ ይገኛል።

ውድድሩ የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በኮማንደር አትሌት ጌጤ ዋሚ ከሚመራው ሂማ ሬስ ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

በሺዎች የሚገመቱ የድሬዳዋ ነዋሪዎች እና የአገራችን ታዋቂ አትሌቶች የተሳተፉበትን የ10ሺ እና የ5ሺ ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ ታዋቂዋ አትሌት ኮማንደር ጌጤ ዋሚ፣ የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊራንኦል ቡልቻ ሌሎች በርካታ እንግዶች ናቸው።

መነሻው ነምበርዋን መድረሻውን ምድር ባቡር አደባባይ ያደረገው "ለፍቅር እሮጣለሁ" የጎዳና ሩጫ ስፖርት መሠረቱ ህብረተሰቡ መሆኑን ለማፅናት ድሬዳዋ በፍቅርና በህብረት ተቻችሎ የሚኖርባት ከተማ መሆኗን ለማሳየት የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነባት ከተማ እና ለኢንቨስትመንት ስራ ያላትን አመቺነት ግንዛቤ በመፍጠር የቀድሞዎቹ ታዋቂ አትሌቶች በስፖርቱና በሌሎች መስኮች መዋዕል ነዋያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ ግንዛቤ ይፈጠራል።

ለሩጫ ውድድሩ ከተዘጋጀው ካኔቴራ እና ሌሎች ተግባራት የሚገኘው ገቢ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ለፈናቀሉ ወገኖች ይውላል።

በታዋቂ ሴቶችና ወንዶች አትሌቶች መካከል የሚካሄደው ውድድር ብርቱ ፉክክር እያስተናገደ ሲሆን አምስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የነዋሪዎች ውድድር አዝናኛ በሆነ መንገድ ተጀምሯል።

በውድድሩ ማብቂያ ለአሸናፊዎች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የዕለቱ የክብር እንግዶች መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም