የአፍሪካ ወጣቶች ለሀገር እድገትና ለህብርተሰብ ለውጥ መትጋትን ከዶክተር አዴሲና እና ከፔትሮ ሳሊኒ ሊማሩ ይገባል

279

ግንቦት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአፍሪካ ወጣቶች ለሀገር ብሎም ለአህጉሩ እድገትና ለህብረተሰብ ለውጥ መትጋትን ከዶክተር አዴሲና እና ከፔትሮ ሳሊኒ ሊማሩ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና እና ለጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በአንድነት ፓርክ በተካሄደው መርሃ ግብር ለተሸላሚቹ የክብር ዶክትሬቱን አበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመርኃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ሁለቱ ግለሰቦች በግብርናው ክፍል ኢኮኖሚና በምህንድስናው ዘርፍ ኢትዮጵያ፣ አፍሪካና ዓለም የተሻለ እድገት እንዲያስመዘግቡ ብርቱ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ዶክተር አኪንውሚ አዴሲና በአፍሪካ ልማት ባንክ አመራርነታቸው የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ የላቀ ሚናቸውን ጠቅሰዋል።

የዊ ቢዩልድ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ ፔትሮ ሳሊኒ፤ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅማሮው እስከ ኃይል ማመንጨት ድረስ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ ወጣቶች ለሀገር ብሎም ለአህጉሩ እድገትና ለህብረተሰብ ለውጥ መትጋትን ከዶክተር አዴሲና እና ከፔትሮ ሳሊኒ የላቀ ሚና ሊማሩ ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልእክታቸው የክብር ዶክተሬት ተሸላሚዎቹ ልምዳቸውን ለትውልዱ እንዲያጋሩ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የግለሰቦቹን ዝርዝር ልምድ በመሰነድ ለትውልዱ የሚተላለፍበትን መንገድ እንዲያመቻች አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር አዴሲና፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ቀጠናዊ የመሰረተ ልማት ትስስስርና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን የማፋጠን ጉዞ ባንኩ በትኩረት የሚያየው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና የአፍሪካም ጭምር መሆኑን ስለምንገነዘብ ድጋፍና እገዛችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ፈተና እያለፈች በተስፋ ጎዳና ላይ መሆኗን የጠቀሱት ዶክተር አዴሲና፤ የክብር ዶክትሬት ሽልማቴ በፅናት ፈተናዎችን ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንልኝ ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቋማ በስኬት ጎዳና እንድትራመድ ማንኛውንም ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተሰማራው የሳሊኒ (We Build) ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፔትሮ ሳሊኒ፤ “ሁለተኛዋ ሀገሬ በሆነችው ኢትዮጵያ ታላቁን ክብር በመሸለሜ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃይል እስኪያመነጭ ድረስ ያደረኩትን አበርክቶ በቀጣይ ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው የልማት ስራዎች የምችለውን ሁሉ ለማበርከት ዝገጁ ነኝ ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ 8ኛው ፕሬዚዳንት በመሆን እየመሩ ያሉት ናይጄሪያዊው አኪዊሚ አዴሲና በአህጉሪቷ የድህነት ቅናሳ፣ የትምህርት መስፋፋት፣ የስራ ፈጠራ እና ሌሎችም ተግባራት ላይ ውጤታማ ስራ ማከናወናቸው ይታወቃል።

በተለይም በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የአርሶ አደሩን ህይወት የሚለውጡ የፈጠራ ቴከኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ከፍትኛ በጀት ለግብርናው ዘር እንዲመደብ በማድረግ ትልቅ ሚና አበርክተዋል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለእኒህ ታላቅ ባለውለታ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

የጣሊያኑ ሳሊኒ (We Build) ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲቪል ስራዎች ግንባታ ስኬታማነት ሃላፊነታቸውን በብቃት የተወጡ ናቸው።

ፔትር ሳሊኒ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለገዳዲ፣ በለስ፣ ኮይሻ፣ ግልገል ጊቤ ከቁጥር አንድ እስከ ሶስት ግድቦች ለሃይልና ሌሎችም ልማቶች እንዲውሉ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

በግድቡ ግንባታ ስኬት የላቀ ሚና ለነበራቸው ለእኒህ ታላቅ ባለውለታ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።

ማህብራዊ ሃላፊነትን በመወጣት ረገድም ድርጅታቸው ለስራ በተሰማራባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል በማቋቋም የአካባቢው ማህበረሰብ አለኝታ መሆናቸውን ማስመስከራቸው ተነግሯል።

በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት አባላትና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።