የክልሉ የወርቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል

114

ጋምቤላ፣ ግንቦት 6/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ያለውን የወርቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

የጋምቤላ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ኤጀንሲ የዕቅድ ክንውን አፈጻጸሙ በአቦቦ ወረዳ በመስክና በመድረክ ትናንት ተገምግሟል።

ኤጀንሲው ከክልሉ ባለፉት አስር ወራት ከ1 ሺህ 150 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን  አስታውቋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ በክልሉ ሕገ ወጥ የወርቅ ንግድ ቁጥጥርና ክትትል በማጠናከር ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልል እስከ ቀበሌ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ባከናወናቸው አበረታች እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን በግምገማ መረጋገጡን ገልጸዋል።

በቀጣይም በግብረ ኃይሉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሀብቱን ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል ጠንክረው እንዲሰሩ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት ሀብቱን በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ተጠቅሞ በማልማት ለክልሉ ብሎም ለሀገር ልማት እንዲውል በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳታ ቻም በበኩላቸው ዘንድሮ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጣውን ወርቅ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ ባለፉት አስር ወራት 1 ሺህ 330 ኪሎ ግራም ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ከ1 ሺህ 150 ኪሎ ግራም በላይ ገቢ በማስገባት የዕቅዱን 91 ከመቶ ማሳካቱን ገልጸዋል።

ለብሄራዊ ባንኩ ገቢ ከተደረገው ወርቅም ከ59 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ አመላክተዋል።

በቀጣይም ዘርፉን በማጠናከር የተሻለ  መጠን ያለው ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመስክና የመድረክ የግምገማ ዓላማውም ይህንኑ ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።

በአቦቦ ወረዳ በሉንጋ ቀበሌ የወርቅ አምራቾች መካከል አቶ ሙሉጌታ ድሪብሳ እንዳሉት በየቀኑ የሚያገኙት የወርቅ መጠን የሚለያይ ቢሆንም፤ በቀን ከአንድ እስከ 10 ግራም ወርቅ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በባህላዊ መልኩ በሰው ጉልበት ብቻ በማምረት የተፈለገውን ያህል ወርቅ እንደማያገኙ የገለጸው ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ወርቅ አምራች ወጣት ኡኩራ አባላ ነው።

በመሆኑም መንግሥት ዘመናዊ የወርቅ መቆፊሪያ መሣሪያ ቢያቀርብላቸው፤ ራሳቸውን ብሎም ሀገርን የሚጠቅም ወርቅ ማምረት እንንደሚችሉ ተናግሯል።

ለክልሉ ባህላዊ የወርቅ አምራቾች የማምረቻ መሣሪያዎች ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ በመስክ ጉብኝቱ ላይ ተናግረዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም