የትምህርት ስርዓቱን ከስፖርቱ ጋር አስተሳስሮ በመቀጠል በአእምሮ የዳበረና በአካል የተጠከረ ትውልድ መገንባት ይገባል

247

ግንቦት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ከስፖርቱ ጋር አስተሳስሮ በመቀጠል በአእምሮ የዳበረና በአካል የተጠናከረ ትውልድ መገንባት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ ተናገሩ።

“በአካልና በአምዕሮው የዳበረ ትውልድ ለሃገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲከሔድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ተማሪዎች የስፖርትዊ ውድድር ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

በውድድሩ አጠቃላይ ነጥብ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አንደኛ ሲሆን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ እንዲሁም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።


በውድድር መርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ስፖርታዊ ውድድሮች ከፉክክር ባለፈ የልምድ መለዋወጫና የአብሮነት መድረኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የትምህርት ስርዓቱን ከስፖርቱ ጋር አስተሳስሮ በመቀጠል በአእምሮ የዳበረና በአካል የጠነከረ ትውልድ መገንባት ይገባል ብለዋል።

ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ፤ ስፖርት አካላዊና አምዕሯዊ ጥንካሬ ያለው ትውልድ በመፈጠር ረገድ የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።


በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት የተካሄደው ስምንተኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ስፖርተረኞች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላት እና ለተወዳዳሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ውድድር የእግር ኳስ፣ ቮሊቮል፣ ጠረጴዛ ቴንስ እና ወርልድ ቴኳንዶ ውደድር ተካሂዷል።