በድሬዳዋ ዘንድሮ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ዝግጅት እየተደረገ ነው

181

ድሬዳዋ፤ ግንቦት 6/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ የደን ልማት ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር   አቶ ከበደ ይማም የተመራ ቡድን ዛሬ በድሬዳዋ   ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን ዘመናዊ የችግኝ ማፍያ ጣቢያና ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ እየተካሄደ የሚገኘውን ዝግጅት ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ  እንዳሉት፤  በፌዴራል መንግስት ድጋፍ በመላው ሀገሪቱ ከተገነቡት ዘመናዊ የችግኝ ጣቢያዎች የድሬዳዋና የጅግጅጋ ይገኙበታል ፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ጣቢያዎች  ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ማፍላት ሂደት  ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ የሚዘጋጁ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ ከጅቡቲ መንግስት ጋር  ያለንን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናከሩ ናቸው ብለዋል።

ለአስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ  150 ሺህ ለጅቡቲ የሚላክና 50 ሺህ ደግሞ ለምስራቅ ተጎራባች ክልሎች በማሰራጨት አካባቢውን  በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር በተቀናጀ መንገድ ይሰራል ብለዋል፡፡

ሀገር በቀል የጥላና የፍራፍሬ ችግኞቹ በገጠርና በከተማ በሚገኙ 26 ችግኝ ጣቢያዎች በድሬዳዋ ግብርና ቢሮና በባለስልጣኑ ቅንጅት እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዱ ናቸው፡፡

እስከ አሁን 1ነጥበ 2 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው፤ የቀሩትም በሚፈለገው ጊዜ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ፣ውሃ ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሊያስ አሊይ በበኩላቸው፤  ችግኝ መትከልና ተንከባክቦ ማሳደግ ለድሬዳዋ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ባለቤት የሌለው ችግኝ እንዳይተከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ለመታደግና  የገጠሩን ህብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን እያገዙ በመሆኑ አጠናክሮ ለመቀጠል እየተሰራ ይገኛል ፡፡

ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከል  ይጠበቃል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት በድሬዳዋ ከተተከሉት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ በአማካይ 62 በመቶ መጽደቃቸው ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም