መንግሥት ሙያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር ጠየቀ

146

አሶሳ ፤ግንቦት 06/ 2914(ኢዜአ) ሚድዋይፈሮች የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጡ መንግሥት ሙያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር ጠየቀ።

30ኛው የዓለም አቀፍ የሚድዋይፈሮች ቀን በሃገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል፡፡

የማህበሩ  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ኃይለመስቀል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤  በኢትየጵያ በሥራ ላይ ከሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ ሚድዋይፈሮች መካከል  57 በመቶው  በዲፕሎማ ደረጃ ትምህርታቸው የተከታተሉ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በዘርፉ የሚሰጠው ስልጠናና ትምህርት በሥራ ላይ ሆነው ደረጃቸውን ለማሻሻል ምቹ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ይህም በሙያው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ተደራሽነታቸው እንዲገደብ ማድረጉን ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥት ሚድዋይፈሮቹ የሙያ ደረጃ የሚሻሽልበትን ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያመቻች  የማህበሩ  ፕሬዚዳንት  ጠይቀዋል፡፡

በክልሎች በሚድዋይፈሮችን የሥራ ምዘናን ደረጃ አሰጣጥ ያተኮሩ ጥናቶች ቢደረጉም ተግባራዊ ሳይደረጉ በመቀመጣቸው ለትግበራቸው ትኩረት ይሰጥ ብለዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ሚድዋይፈሮች ሀገር ችግር በገጠማት ወቅት ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣታቸው ምስጋናና አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የሚድዋይፈሮች የሙያ ደረጃ እድገት፣ ማሻሻያና ጥቅማጥቅም እንዲከበር እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

''ሚድዋይፈሮች የሚያገኙት ሙያዊ ክፍያ በሚያገለግሉት ልክ እንዳልሆነ መንግሥት ይረዳል፤ የህጻናትና እናቶችን ህይወት በመታደግ በምታገኙት የህሊና እርካታ ልትኮሩ ይገባል'' ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም የጨቅላ ህጻናትን ሞት በመቀነስ  ውጤታማ ቢሆኑም፤ ሚድዋይፈሮች ሙያዊ ድጋፋቸው እንዲያጠናክሩ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ፤በክልሉ ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ አገልግሎት ሚድዋይፈሮች የሚያደርጉት እገዛ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በጸጥታ ችግር የወደሙ ጤና ተቋማትን ለማሟላት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጥረት በተጓዳኝ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

 የሚድዋይፈሮች ቀን ምክንያት በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ሚድዋፈሮች እንዲሁም ለሙያው መጠናከር አስተዋጽኦ ያደረጉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የሁሉም ክልሎች የሚድዋይፈሮች ማህበራት፣ የፌዴራል መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አመራሮች መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም