የቦሌ ክፍለ ከተማ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት እድሳት ጀመረ

139

ግንቦት 6 ቀን 2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የቦሌ ክፍለ ከተማ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት እድሳት ጀመረ።

ክፍለ ከተማው በዘንድሮው ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ300 በላይ የአቅመ ደካማ ወገኖችን መኖሪያ ቤቶች ለማደስ አቅዷል።

ለዚህም ሁሉንም ማኅበረሰብ፣ ተቋማት እና ድጋፍ ማድረግ የሚሹ ወገኖችን ተሳትፎ ይጠይቃል።

በክፍለ ከተማው የመኖሪያ ቤታቸው እድሳት ከተጀመረላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ቆንጂት ሸዋዬ አራት ልጆቻቸውን ይዘው በሴፍትኔት እየተደገፉ አስቸጋሪ ኑሮ ይገፋሉ።

በዝናብና ፀሐይ እየተፈተኑ ጣሪያና ግድግዳዋ በተዛነፈው ቤታቸው የሚኖሩት ወይዘሮዋ የሚጠግንላቸው ወገን ይሹ ነበር።

በመሆኑም በዚህ ክረምት ቤታቸው ከሚታደስላቸው እድለኞች መካከል አንዷ በመሆን በዛሬው እለት ሥራው ተጀምሮላቸዋል።

የቤታቸውን እድሳት መጀመር በተመለከቱ ጊዜ የተሰማቸው ደስታ ወደር የሌለው መሆኑን ይናገራሉ።

የቤት እድሳት የተጀመረላቸው ሌላኛዋ የክፍለ ከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ጣይቱ ሐሰንም በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ቤታቸው በክረምት ዝናብ በበጋ ደግሞ ፀሐይ የማይከላከልላቸው ያረጀ መሆኑን ተናግረው፤ ሊታደስልኝ በመሆኑ ለበጎ ፈቃደኞቹ ምስጋናዬ ይድረስ ብለዋል።

ስድስት ሆነው የሚኖሩባት ቤት ከጥበቷ በተጨማሪ የክረምቱ ዝናብ ይፈትናት እንደነበር ያስታወሰችው ልጃቸው ቦሰና ሰኢድ እድሳቱ በመጀመሩ ደስታችን ወደር የለውም ብላለች።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለምፀሐይ ሽፈራሁ፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ አረንጓዴ አሻራን ማኖርና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በዛሬው እለት በክፍለ ከተማው ባሉ ወረዳዎች በይፋ የተጀመረው የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትም ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በክፍለ ከተማው የቤት እድሳት መርሃ-ግብር ከ300 በላይ ቤቶች እድሳት የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።

ከ40ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በመለየት ከ31 ሺህ በላይ ለሆኑት የማዕድ ማጋራት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም