ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ በአገርም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ይሻል

136

ግንቦት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለከፋ እንግልትና ጉዳት እየዳረገ በአገርም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየ15 ቀኑ የሚካሄደው ”ጉሚ በለል” 22ኛው ዙር መድረክ ትኩረቱን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በማድረግ ተካሂዷል።

በመድረኩ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ከአምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተጨማሪ ከፌዴራል ተቋማትና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በኦሮሚያ ክልል ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለና አገራዊ ችግር መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል።

ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይም በታዳጊ አገሮች ላይ በስፋት የሚስተዋለው ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ መሆኑ ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያም በርካታ ዜጎች በሕገ-ወጥ መልኩ መሰደድ ዋነኛው ምክንያት በሥራ-አጥነት ሳቢያ የእለት ኑሮ ክብደት መሆኑ በመድረኩ ላይ ተወስቷል።

ከሥራ-አጥነት በተጨማሪ የሕገ-ወጥ ደላሎች መበራከትና ስደትን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድም ለዜጎች በሕገ-ወጥ መልኩ መሰደድ ምክንያቶች መሆናቸው ተመላክቷል።

በመሆኑም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተለይም ለወጣቶች ሥራ በመፍጠር ሰርተው በመለወጥ ለራሳቸውም ይሁን ለአገር እንዲጠቅሙ ማስቻል ይገባል ተብሏል።

የሕገ-ወጥ ስደትን አስከፊነት በስፋት ማሳወቅ እንዲሁም በሕገ-ወጥ የድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ማድረግም በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገልጿል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለከፋ እንግልትና ጉዳት እየዳረገ ለአገርም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ዘላቂ እልባት ሊበጅለት ይገባል ተብሏል።

ለዚህ ደግሞ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አገራዊ ችግር ሆኖ በመቀጠሉ መፍትሔ ለመሻት የመንግሥት ጥረት እንዳለ ሆኖ የሁሉንም አካላት ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዜጎች በህጋዊ መንገድ ብቻ ወደ ሌሎች አገሮች ተዘዋውረው እንዲሰሩ ማመቻቸትም አንዱ መፍትሔ ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለዚህም ከአገራትና የተለያዩ ተቋማት ጋር ህጋዊ ስምምነት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ በተለይም የወጣቶች የሥራ ባህልና ሰርቶ የመለወጥ እምነት በደንብ መቃኘት ይኖርበታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️