አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱ በጥናት ተመላከተ

157

ግንቦት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመበት ወቅት 288 ቢሊዮን 16 ሚሊየን 448 ሺህ 452 ብር ግምት ያለው ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ጥናት አመለከተ።

ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱ ጥናቱ በዝርዝር አመላክቷል።

አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ያደረሰው ጉዳት በተመለከተ ጥናት ሲያደርግ የነበረው ቡድን የጥናቱን ጥቅል ውጤት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

አምስት ወራት በፈጀው በዚህ የጉዳት መጠን ጥናት ውስጥ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልሉ መንግስትና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ተሳትፈዋል።

በጥናቱ አሸባሪው ህወሃት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በዚህም የንጹሃንን ህይወት ማጥፋትን ጨምሮ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ አሳይቷል።

የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች 1 ሺህ 782 የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መፈጸማቸውን የገለጸው የጥናቱ ውጤት፤ በቡድን በመሆን በቤተሰብ አባላት ፊት አስገድዶ የመድፈር ድርጊት በመፈጸም አሰቃቂ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል።

ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች 6 ሺህ 985 የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎችን በጦርነቱ ምንም አይነት ተሳትፎ ሳይኖራቸው በጅምላና በተናጥል እንደረሸናቸው ጥናቱ ማረጋገጡን የቡድኑ አባላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም