“የጋራ ትብብራችን ከተጠናከረ የማንፈታው ችግር፤ የማናልፈው ፈተና አይኖርም”- ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

70

ግንቦት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋራ ትብብራችን ከተጠናከረ የማንፈታው ችግር የማናልፈው ፈተና አይኖርም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የ250 አቅመ ደካማ ወገኖችን መኖሪያ ቤት የማደስ መርሃ- ግብር በዛሬው እለት አስጀምረዋል።

በዚህ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት፤የዜጎችን ሁለንተናዊ ችግሮች ለማቃለል የጋራ ጥረታችን፣ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴታችን አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝ እና አቅመ ደካሞችን መንከባከብ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን በጋራ የምናከናውነው የበጎነታችን ማሳያ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ”የከተማዋ ነዋሪዎች፣ባለሃብቶች፣በውጭም በአገር ውስጥም ያላችሁ ወገኖች በጎ ተግባራትን በመፈጸም የሰብአዊነት አሻራችንን እናሳርፍ”ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“የጋራ ትብብራችን ከተጠናከረ የማንፈታው ችግር የማናልፈው ፈተና አይኖርም” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታዬ መሐመድ፤ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ባለሃብቶች የተቸገሩ ወገኖችንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክፍለ ከተማው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት መጀመሩን ጠቅሰው፤ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የመኖሪያ ቤት የማደስ ሥራው የክረምቱ ወቅት ሳይገባ እንዲጠናቀቅ ርብርብ እናደርጋለን ብለዋል።

በክፍለ ከተማው ከቤት እድሳት በተጨማሪ ሌሎች በጎ ተግባራትን የማከናወን እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ለዚህም የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤት እድሳቱ ከተጀመረላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ ዙልፋ ኢላላ፤ የክረምቱ ወቅት በመጣ ቁጥር በችግርና ሰቀቀን ይሰቃዩ የነበረ ቢሆንም ቤታቸው ታድሶ ሊኖሩበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የእርሳቸውን ችግር በመረዳት እድሳቱን ለጀመሩላቸው ወገኖችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ምክትል ከንቲባው የቤት እድሳቱን ከማስጀመር ጎን ለጎን በክፍለ ከተማው በ70 ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 2 ሺህ 233 ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ቁልፍ አስረክበዋል፡፡

የመስሪያ ቦታ የተረከቡት ወጣቶች ሰርተው ራሳቸውን ለመለወጥና ለሌሎችም ለመትረፍ በትጋት እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በዘንድሮው ዓመት በመዲናዋ ለ350 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️