አሜሪካ ያደገችው በማበረታቻ ነው፤ ኢትዮጵያስ…?

112
በእንግዳው ከፍያለው ከባ/ዳር ኢዜአ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ዘንድሮ በመደበኛው የ2ኛ ዲግሪ ሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ትምሀርት ዘርፍ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ሻፈር የሚባል አሜሪካዊ ፈረንጅ ያስተምረን ነበር። የሚያስተምረን የትምህርት ዓይነቱም “ኮምዩኒኬሽን ፎር ዴቨሎፕመንት” የሚል ነው። ፕሮፌሰሩ ሁሌም ሲያስተምር ጥያቄ ይጠይቃል። በመንገድ፣ በካፌ፣ በሆቴልና በየትኛውም ቦታ ሁሉ ያጋጠመውን ሁነት እያመጣ በጥያቄ መልክ ለተማሪዎቹ ያቀርባል ። ሴቶች ባጃጅ ሲያሽከርክሩ አየሁ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስሄድ ሰው ተጨናንቋል ። እኔን ግን ውስጥ አስገብተው አስተናገዱኝ ለምን? ባህርዳር ብዙ የምዕራባውያን ምግብ ቤቶች የሉም ለምን?… የሚሉ ሃሳቦችን ያነሳል። በዓለም ላይ የመጨረሻው የሚጣፍጥ መጠጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን እሱም “ጠጅ” ነው ። በዓለም ላይ በጣም ዋጋው ዝቅተኛ የሆነው መጠጥም የሚገኘው ኢትዮጵያ ነው ። እሱም “ጠላ” ነው ይላል። “ጠላ” በአምስት ብር ነው ባህርዳር ቀበሌ አራት የሚሸጠው። የሚሸጥባቸውን ቤቶችም ይዘርዝራቸዋል። እንዴት ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱን አካባቢ ከነ መጠጡ፣ ከነምግቡ… እንዳወቀው ያስደንቃል። እሱ የሚዘረዝራቸውን የጠላና የጠጅ ቤቶች እኛ ስለማናውቃቸው ይገርመናል። በጣም ይጥማል ለምን ድራፍት፣ ቢራ… ትጠጣላችሁ እያለ ከእድገት ጋር እያያዘ ይጠይቃል። የሚጠይቀው ነገር ለእኛ አንዳንዴ ተራ ይመስለናል ። ነገር ግን በሂደት የተማርኩት ነገር እያንዳንዷ ነገር የምናያት፣ የምንሰማት፣ የምንዳስሳትና ምን አልባትም ሊሆን ይችላል ብለን የምንስበው ሁሉ ለታላላቅ ሃሳቦች መነሻ መሆኑን ከፕሮፌሰሩ መማር ችያለሁ። በጋዜጠኝነት ሙያ ደግሞ እያንዳንዳንዷን የህዝብ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ማየት፣ መፈተሽ፣ መመርመር፣ እውነተኛነቱን ማረጋገጥና መዘገብ ለአፍታም የሚዘነጋ ባለመሆኑ ጠቃሚ ነው። ከዕለታት አንድ ቀን ፕሮፌሰር ሪቻርድ ከማስተማሪያ ክፍሉ ገባና ትናንት አንድ ሆቴል ላይ ቁጭ ብዬ የኢትዮጵያውያንን የባህል ልብስ የለበሰች ሴት መጣች በማለት የተለመደ ወሬውን ጀመረ። እሷ ስትመጣ አስተናጋጆቹ፣ የሚያስተባብሩት፣ ባለቤቶቹ፣ ከኩሽና የሚሰሩት ሁሉ እየወጡ ተራ በተራ ሰላም አሏትና ወንበር ሰጥተዋት ተቀመጠች። “እነሱም ከበዋት ለረጅም ጊዜ እያወሩ ይሳሳቃሉ። እኛን ማስተናገዱን እስኪረሱት ድረስ ነበር ናፍቆታቸው በተመስጦ የሚያወሩት። ይስቃሉ፣ ያወራሉ፣ ይስቃሉ… ” አለ ፕሮፌሰሩ። እኛም ቀልባችን ገዝተን እንሰማለን። እንሰማለን ስል ያለብን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችግር ከሰውየው የአነጋገር ቅላጼ ጋር ተያይዞ ለአንዳንዶቻችን ምን እንደሚል በሙሉ የሚሰማን አለመሆኑ ግልጽ ነው። ለአንዳንዶቻችን ደግሞ አልፎ አልፎ የምንሰማትን ቃላት ከሌላው ጋር በማገናኘት አጠቃላይ ጽንሰ ሃሳቡን ለመረዳት እንሞክራለን። ቀልጠፍ ብለው ሁሉንም ሃሳብ ሰምተው የሚረዱም አሉ። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ቀጠል አደረገና አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ አለ። ወይ ጉድ ልንማር ሄደን፣ ወንበር ላይ ተቀምጠን… አንጠየቅም አንል። ይሁንታችንን በዝምታ ገልጽንለት። በእርግጥ ዝምታ ተቃውሞም ሊሆን ይችላል። ዘግየት ብለንም ቢሆን ፈቃደኝነታችን አንገታችንን ነቅነቅ አድርገን ገልጽንለት። “ያች በባህላዊ ልብስ ዘንጣ ስትመጣ ከባለቤቱ ጀምሮ ሁሉም ሰራተኛ ተራ በተራ እየሳመ፣ እያቀፈ.…፣ ከቦ…. ሲያወራት የነበረች ሴት ምን ልትሆን ትችላለች? መላ ምታችሁን አስቀምጡ” አለ ፊቱን ወደ ሰሌዳው እየመለሰ። አንዷ ተማሪ እጇን አወጣች፤  “እሽ” በማለት እንድትመልስ ፈቀደላት። እኛ ኢትዮጵያውያን ሰውን በክብር መቀበል ባህላችን ስለሆነ ነው አለች። “አይደለም ሌላ” አለ ቆፍጠን ብሎ። አንዱ ባህላችን ነው ማስተናገድ ሲል ሌላው ሌላ ሲል የልቡ አልድርስለት ስላለ የኤክስ ምልክት በቀኝ እጁ እየሰራ አይደለም ይላል። በመጨረሻም አንዱ ተማሪ እጁን አወጣ። “እሽ  ቀጥል” አለው። ምን አልባት ያች ሴት ቀደም ሲል ከሆቴሉ በአስተናጋጅነትም ሆነ በሌላ የስራ መስክ ስትሰራ ቆይታ አሁን ላይ በትዳር ወይም የተሻለ ስራ በማግኘት ወደ ሌላ አካባቢ ሄዳ ቆይቶ አሁን ልትጠይቃቸው መጥታ ይሆናል ብሎ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ “በትክክል … /ዩ ጌት ፋይፍ ብር/ አምስት ብር ለመለስከው አግኝተሃል” አለ። እኛ በሳቅ ወደቅን። ምክንያቱም የዛሬን አምስት ብር ዋጋ እስኪ አስቧት ። ደግሞ ከፈረንጅ አፍ የአምስት ብር ድምጽ ሲወጣ፣ ከፈረንጅ ኪስ አምስት ብር ስትወጣ.. መስማትና ማየት እንዴት አያስቅ፣ በደንብ ያስቃል እንጂ ። ተንከተከትን፣ እያረፍን እንደገና ተሳሳቅን… ተንከተከተን። ፕሮፌሰሩ ነገሩ ገብቶት ቆይቶ እንዴ ለምን ትስቃላችሁ? “አሜሪካ ያደገችው በማበረታቻ ነው ። ብሩ አነሰ ከሆነ ማበረታቻ አነሰም በዛ ያው ማበረታቻ ነው” በማለት ደገመ። “እንዳውም እናንተ ኢትዮጵያውያን የማበረታት ባህላችሁ ደካማ ስለሆነ የማታድጉት፣ የማትለወጡት፣ የማትበለጸጉት…” ብሎን እርፍ። “በል ቻለው ሆዴ…” ነው ያለው ዘፋኙ/ኟ። በአእምሯችን እነዚህ ነጮች ግን ለኛ ያላቸው ንቀት ከፍተኛ ነው ብለን ሁላችን በአእምሯችን ስናብሰለስል  ክፍለ ጊዜው አልቆ መውጣት ስንጀምር ሁላችንም ማውራት የጀመርነው እንዴት ነው እኛን የሚያየን? አምስት ብርን ገንዘብ ብሏት ነው… የሚሉና ሌሎች ሃሳቦችን ሁላችንም እየተለዋወጥን ከክፍሉ ወጣን ። ፈረንጁም አምስት ብር መስጠት ስለተሳቀበት አፍሮ ነው መሰል ለመለሰው ተማሪ ከአሜሪካ የመጣለትን “የኒውስ ታይምስ” መጽሄት “በአምስቱ ብር ፋንታ ይኼን ሸልሜሃለሁ” ብሎ  ሰጠው። በሌላ ቀን ደግሞ ኢትኖግራፊክ ጥናት እንድንሰራ አዘዘን። ሲያዘን በአካቢያችሁ የማህበረሰብ ችግር፣ ባህል፣ ከእድገት ጋር ተያይዞ የመጣ ለውጥ ላይ ብታተኩሩ ጥሩ ነው አለን። እንሞክራለን እንጂ ወዴት ይደረሳል አልን በልባችን። “ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡት ለእያንዳንዳቸው 600 ብር እሸልማለሁ” ገና ከማለቱ ሁላችንም ሳቃችንን ለቀቅነው። ፕሮፌሰሩም “ስንቴ ልንገራችሁ አሜሪካ ያደገችው በኢንሴንቲቭ/ በማበረታቻ/ ነው አልኳችሁ እኮ” አለ ፈርጠም ብሎ። ፊቱንም ከወትሮው በተለየ መልኩ አኮሳትሮታል። እኛም የአገራችን መምህር ቢሆን እንደዚህ ባልሳቅን፣ አነሰም በዛ ነጻነት የሚሰጠን፣ ሃሳባችን ለመረዳት የሚሞክርልን እሱ በመሆኑ ነው በሳቅ የምንዝናናው ፣ የምንደሰተው፣ ልባችን በሃሴት የሚፈነድቀው…በእሱ ክፍለ ጊዜ ነው። የሚገርመው ሁሉም ሰው በስራው መብዛትና በፈተና የተጨናነቀ ስለነበር ማንም ፈረንጁ የገባውን ቃል ከክፍል ከወጣን በኋላ ያስታወሰው አልነበረም። ፈረንጁም ቀድሞ ወደ አገሩ ስለሄደ ሳቃችን እንኳ ረስተነዋል። ለካስ ፈረንጅ ቃሉን ጠባቂ ነው የሚባለው እውነት ነው። 1ሺ200 ብር የሚዲያና ኮምዩኔኪሽን ዲፓርትመንት ሃላፊው ጋ አስቀምጦ ሂዷል። በኋላ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የወጡትን ስም ዝርዝር በኢሜይል ለትምህርት ክፍል ሃላፊው ልኳል።    ባጋጣሚ አንደኛ ያመጣው የሆቴሏን ሴት ጥያቄ የመለሰው ነበርና 600 ብር ወሰደ። ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡት ደግሞ 300 ብር ለእያንዳንዳቸው ተሰጣቸው። የፕሮፌሰር ሪቻርድን የማስተማር ስልት ያመጣሁት አሁን ከአገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ስለተያያዘብኝ ነው። ለምን? እንዴት?…? አትሉም። ነገሩ እንዲህ ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ ተገኝተው ነበር። ከወረዳ እስከ ክልል ለተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ለሚሆኑ አመራሮች “በፓዎር ፖይንት” የታገዘ ስልጠና ለአመራሩ ሰጥተዋል። አቢይ በተፈጥሮውም ሆነ በልምድና በእውቀት ካገኘው ባላውቅም ታዳሚን ማሳቅና ማስጨብጨብ የተሳካለት መሪ ነው። ንግግሮቹም ልብ ብሎ ላዳመጣቸው ሰው ፈረንጆቹ/ Rehetoric/ የሚባለው ዓይነት ነው። ተሳታፊውም ዘና ብሎ ነው የሚከታተለው በቀልድ፣ በስነ ቃል፣ በተረትና ምሳሌ በማስደገፍ ስለሚያስተምር። “አሁን አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ … ጥያቄውን የመለሰ የራሴን ሽልማት አዘጋጅቻለሁ” አላቸው ለተሳታፊዎቹ። እንኳን ሽልማት ሰላምታውን የሚናፍቀው ታዳሚ በሙሉ ልብ ቀድሞ ለመመለስ አእምሮውን፣ ልቡንና ቀልቡን ገዝቶ ጸጥ አለ። የጠቅላይሚንስትሩን የሽልማት ትርፋት ለመቅሰምም ጸሎት አይሉት ልመና ሁሉም ሰው በልቡ ማሰቡን ቀጥሏል። “ጥያቄው…” አለ ጠቅላይ ሚንስትሩ የተለመደ ፈገግታውን እያሳየ። ሁሉም ተሳታፊ አንገቱን ከፍ ከፍ አደረገ ከአዳራሹ አየር መልስ የሚገኝ ይመስል። ጥያቄው “የሚገዛኝ አይጠቀምብኝም፤ የሚጠቀምብኝ አያየኝም፣ እንደተጠቀመብኝም አያውቅም” የሚል ነው አለ ዶክተር አቢይ። ሁሉም ተሳታፊ ማውጣት ማውረዱን ተያይዞታል። ወደ ጎን መንሾካሾክም ተጀምሯል። እጅ ፈጥኖ የሚያወጣ ግን አልተገኘም። መቼም ያልሆነ መልስ ተናግሮ ከ2ሺህ በላይ አመራር በሞላበት አዳራሽ መሳቂያ መሳለቂያ መሆን የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። በደንብ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ ከተቻለ እርግጠኛነቱን ከጎን ካለ ጓደኛ ጋር መምከርና መመለስ ተገቢ ነው። መልሱም የሚሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻዋል። የልጆች ተረት ተረት አይደለም። ከጥቂት ዝምታ በኋላ ከኋላ አካባቢ አንድ ታዳሚ እጁን አወጣ። “እሺ ተነስና መልስ” አለው ዶክተር አቢይ። መልሱ… ሲል የሁሉም ሰው ልብ ትርታ ጨምሯል። ያገኘዋል ወይስ አየገኘውም በሚል ጥርጣሬ የተሞላበት ጭንቀት። “መልሱ”  “የሬሳ ሳጥን” ነው አለ። “በትክክል መልሰኸዋል” ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም አጨበጨበ። ቀጠለና “አሁን ጥያቄውን የመለስከው ወጣት አመራር አድራሻህንና ሙሉ ስምህን ትሰጠናለህ። በቅርቡ ለጉብኝት ቻይና  የሚሄዱ ከፍተኛ አመራሮች አሉ። አንተም ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሄደህ የመጎብኘት እድል አግኝተሃል። እንኳን ደስ አለህ” ብሎት እርፍ። እኔ እንደ አምስት ብር ዝቅ ያለች ሽልማት ስጠብቅ በአንድ ጥያቄ መልስ አንዱ ጓደኛዬ የቻይና ጉብኝት ሽልማት አግኝቶ መጣ እላችኋለሁ። ዶክተር አቢይ ስለቻይና እያወራ በአእምሮዬ የመጣብኝ የፕሮፌሰር ሪቻርድ የማበረታቻ/ኢንሴንቲቭ  አባባል ነው። ደግሞ ደጋግሞ “አሜሪካ ያደገችው በኢንሴንቲቭ ነው” የሚለው አባባል። ምን አልባት ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአሜሪካኖችን ስልት እየተከተለ ይሆን እንዴ? አልኩኝ። አንተ የምንለው ፍቅራችንን ለመግለፅ ሲባል ነው ። ባለፈው ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በወርቅ የሚመረቁት መንግስት ስኮላር ሽፕ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባው ገና ቀድሞ ሳይመረቁ ነበር። የእርሱን ቃል የሰማው ተማሪ ሁሉ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ጠንክሮ እንዲማር መነሳሳትን መፍጠር ጀምሯል ። “የመንግስታችን አንዱና ዋናው ችግር ያጠፋን የሚቀጣ እንጂ ጥሩ የሰራን የሚያበረታታ ህግ ወይም ስርዓት የለንም ። የረፈደን የሚቀጣ ህግ ግን በሽ ነው” ሲሉም በርካቶች ይደመጣሉ ። በተለይም ለምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ በኪነጥበብና ሌሎች ለየት ስራዎች ለተሰማሩት ተስፋ ሰጭ አቅጣጫ ነው - አዲሱ የማበረታቻ እይታ። ማበረታታትን የሚጠላ የለም እና ለመሸለም ሌት ከቀን ሰው መስራቱ ደግሞ የሰው ሰብኣዊና የተፈጥሮ ህግ ነው። ለነገሩ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ማበረታታትን ብቻ ሳይሆን ችግር የገጠማቸውን የማስተዛዘን ማህበራዊ ሃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት ለሁሉም ሰው አዲስ ተስፋ ይዞ ብቅ ብሏል። የታመመን ይጠይቃል።  የሞተን ቤተሰቡን ያጽናናል። ችግር ውስጥ ያለን ከስቃዩ ለማውጣት የራሱን  ፈጣን ምላሽ ያፈላልጋል ። ባለፉት አራት ወራት በሁሉም የተሳካ ውጤት አሳይቷል። መሪ ማለት የተገለለ ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጋር በክፉውም በደጉም የሚገናኝ መሆኑን ሰሞኑን ባህርዳር ሲመጣ ቀጥታ ከብአዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ከነበሩትና በቅርቡ ህይወታቸው ካለፈው ከአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ቤት በመገኘት የሃዘን ተካፋይ በመሆን ታላቅ ስብዕናውን አስመስክሯል።። ቤተሰቡንም አጽናንቷል። በዚህ ዘመን የሟችን ልጅን አቅፎ፣ ስሞ፣ ዳብሶ… የሚያበረታታ መሪ የት ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህ የተቀደሰ ተግባሩን  ሳውዲ አረቢያ በሄደበት ወቅት በህክምና ስህተት ምክንያት የአልጋ ቁራኛ የሆነን ወጣት  በመጠየቅ ቤተሰቡን በማጽናናት አስፈላጊው ካሳ ተከፍሏችሁ በቅርቡ አገራችሁ  ትገባላችሁ ከማለት በላይ ምን አይነት አዛኝነት?... ርህራሄ? …አጽናኝነት? …አበረታችነት?… ? ሊኖር ይችላል። ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ካሳ አግኝተው ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው። በሰኔ 16/2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በቦንብ ተጎድተው ሆስፒታል የገቡትን ሆስፒታል ድረስ በመገኘት ጠይቋል፣ ደም በመለገስ አጋርነቱን አሳይታል፣ የሞቱትን ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ደውሎ እንዳጽናና በሚዲያዎች ተዘግቧል። አገራችን አሁን ላይ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኑ ግልጽ ነው። ይዞ የመጣው አዲስ ነገር ደግሞ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መደመርን… ነው። ለአገር አንድነትና ሰላም መጠናከር ምሰሶ የሆኑት ፍቅር፣ መቻቻል፣ መዋደድ፣ መደመር… እንደ እሴት ዳብረው እንዲቀጥሉ አዲሱ አገራዊ አቅጣጫ ጥሩ የሰራውን የማበረታት፤ መጥፎ የሰራን መውቀስ ባህል መደረግ አለበት። የአሜሪካኖች ኢንሴንቲቭ አካሄድ ስልት በአገራችን ከቀጠለ ኢትዮጵያውያን ባለን ሞራላዊ ልዕልናና ወኔ የማንወጣው ዳገት፣ የማንሻገረው ሸለቆ፣ የማንወርደው ቁልቁለት… እንደማይኖር አባቶቻችን በአድዋ የፈጸሙት አኩሪ ገድል ምስክር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም