በክልሉ የተካሄዱ የውይይት መድረኮች ዜጎች በሀገር ግንባታው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መነሳሳትን ፈጥረዋል

91

ሐዋሳ፣ ግንቦት 05/2014 (ኦዜአ)..በሲዳማ ክልል በየደረጃው ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተካሄዱ የውይይት መድረኮች ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች የጠራ ግንዛቤ አግኝተው በሀገር ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መነሳሳት መፍጠራቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የውይይት መድረኮቹ አካል የሆነው ”የዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሁለንተናዊ ብልፅግና! በሚል መሪ ሀሳብ ከመገናኛ ብዙኃንና ኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የተካሄዱት መድረኮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የጠራ ግንዛቤ አግኝተው በሀገር ግንባታ ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መነሳሳትን ፈጥረዋል።

ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በክልሉ በሁሉም ወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በተዘጋጁት በተካሄዱት የውይይት መድረኮች የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደረጎባቸው ለተነሱ ጉዳዮች ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።

በመድረኮቹ ህብረተሰቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በሀገር ሰላምና ግንባታ የጋራ አቋም መያዙን አስታውቀዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በየደረጃው በተካሄዱ መድረኮች ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፍትህ አካላት፣ ሴቶች፣ መምህራንና የማህበረሰቡ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በመድረኮቹ በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ የሠላም እጦት፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት፣ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና በሌሎችም ጉዳዮች ውይይ ተደርጓል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራር አቶ ዓለማየሁ በላይ በመድረኩ ላይ የመገናኛ ብዙኃንና ኮሙዩኒኬሸን ባለሙያዎች ለሀገር ሰላም፣ ለዜጎች አብሮነትና አንድነት እሴት መጠናከር ያላቸውን ጉልህ ድርሻ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በተለይም ሀገር ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ለህዝቡ ወቅታዊና ተገቢ መረጃ ተደራሽ በማድረግና በማነሳሳት ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቁ ገንቢ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

አሁንም ሀገሪቷ ካጋጠማት የተለያዩ ተጽዕኖዎችና ችግሮች እንድትላቀቅ ህዝቡን ዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ ሀገሪቷን ለመታደግ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አቶ ዓለማየሁ አሳስበዋል።

በወጣቱ በጊዜያዊ አጀንዳዎች እንዳይጠመድና በሀገር ጉዳይ የጠራ አመከካከትና ግንዛቤ ይዞ ለሀገር ሰላምና አንድነት ዘብ እንዲቆም ሚዛናዊ ዘገባዎች በማቅረብ በአርአያነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሙያቸውን ተጠቅመው ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ዜጎች ለሀገር ሠላም፣ አንድነትና ልማት በጋራ እንዲተጉ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተለይ አሁን ላይ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ፣ በኃይማኖቶች መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርጉ አካላትን ሴራ በማጋለጥና በፅናት በመታገል ለህዝቦች ብልጽግና ለመስራት እንደተነሳሱ ተናግረዋል።