ገጣሚና ጸሃፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የሚውሉ የተለያዩ መጽሃፍትን ለኢዜአ አስረከቡ

222

ግንቦት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ገጣሚና ጸሃፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የሚውሉ የተለያዩ መጽሃፍትን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አስረከቡ። 

ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት የመጽሃፍት ድጋፍ በማድረግ ዕውቀትን ለተተኪው ትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባ የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ተናግረዋል።

በእውቀት የታነጸ ትውልድን በማፍራት የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የንባብ ባህልን ማሳደግ እና ዘመናዊ የንባብ ማዕከላትን መፍጠር ሁነኛ መሳሪያዎች ናቸው።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የአብርሆት ቤተ መጽሃፍትም ይህኑ ዓላማ በማንገብ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ቤተ መጽሃፍቱን በተለያዩ መጽሃፍት ለማደራጀትም ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ የማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል።

ስራውን ለማሳካትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ኪነጥበባት ቢሮ፣ ከደራሲያን ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተውጣጡ አካላት በኮሚቴነት እየመሩት ነው።

መርሃ ግብሩን ለማሳካት የተለያዩ ተቋማት ተሳትፏቸውን በማጠናከር መጽሃፍትን አሰባስበው እያስረከቡ እንደሆነ ይታወቃል።

ኢዜአም ግዙፉን የአብርሆት ቤተ መጽሃፍ ለማደራጀት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የተለያዩ መጽሃፍቶችን በማሰባሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም ገጣሚና ጸኃፈ ተውኔት አያልነህ ሙላት በኢዜአ በኩል ለአብርሆት ቤተመጽሃፍ እንዲውሉ በማሰብ የተለያዩ የእጅ ድርሰቶችን ለግሷል።

በዚሁ ወቅት የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ገጣሚና ጸኃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት እንዲውል ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

መጽሃፍትን መለገስም የተሻለ ነገን መመልከት የሚችል በእውቀት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በእውቀት የታነጸ ሰው ለተደራስያን መጽሃፍትን ማበርከቱም ተጨማሪ በእውቀት የተገነባ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚረዳ አንስተዋል።

መጽሃፍትን ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት በማበርከትም ዕውቀትን ለተተኪው ትውልድ የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል።

ገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ መኖሪያ ቤት በርካታ መጽሃፍት መኖራቸውን ገልጸው፤ የተበረከቱትን መጽሃፍትም ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በኢዜአ በኩል በስማቸው ይበረከታሉ ብለዋል።

"መጽሃፍት እጄን ይዘው ዓለምን አዙረው አሳዩኝ" እንዲሉ መፃፍና ማንበብም ዓለምን የማያ ወሳኝ መንገዶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ለአብርሆት ቤተመጽሃፍት እንዲውል ለኢዜአ ያስረከቡት የእጅ ድርሰቶችም ለበርካታ ኢትዮጵዊያን እንዲደርስ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዘመናዊ መልኩ የተገነባው የአብርሆት ቤተ መፃህፍት ሶፍት ኮፒን ጨምሮ ከ4 ሚሊዮን በላይ መጽሀፍቶችን የመያዝ አቅም አለው።

ቤተ መጽሃፉም በጠቅላይ ሚኒስትር በዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም