ሁሉም አካላት ከራስ ፍላጎት ወጥተው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው

110

መቱ፣ ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ) ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር ሁሉም አካላት ከራስ ፍላጎት ይልቅ ብሄራዊ ጥቅምን አስቀድመው ለስኬታማነት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ሲሉ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ሀገራዊ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ከትናንት በስትያ ተካሂዷል።

የኮንፈረንሱ ተሰታፊ ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ነው።

ምሁራኑ እንዳሉት እንደ ሀገር ያሉብንን ሁለንተናዊ ፈተናዎችና ችግሮች ሁሉም አካላት በጋራ በመነጋገር መፍታትን መለማመድ ያስፈልጋል።

የሀገሪቱን ችግሮች ባልተገባ መንገድ እንፈታለን ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ከራሳቸው ፍላጎት ወጥተው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አየነው ብርሃኑ ለሀገር ሕልውና መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በግልፅ ተወያይተን የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።

ዶክተር አየነው እንዳሉት ባንዲራ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ የወሰንና ድንበር እንዲሁም የቋንቋና ሌሎች የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች ለማጥበብ ብሔራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው።

"ከምክክርና ውይይት ውጭ የጦር መሣሪያንና ጦርነትን ወይም ኃይልን ለችግሮች መፍቻ መንገድ አድርጎ መጠቀም ሀገርን ከችግር ወደ ሌላ ውስብስብ ችግር ማስገባትና ወደ ኋላ መመለስ ነው" ብለዋል።

መንግሥት በጉዳዩ አስፈላጊነት ዙሪያ እያሳየ ያለው አቋምና ዝግጁነት፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይሁንታና ድጋፍ ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር እንደ ጥሩ ዕድሎች የሚታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካላት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ሲሉም ዶክተር አየነው አስገንዝበዋል።

መንግሥት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሀገር ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ለሀገራዊ ጥቅም መቆማቸውን በተግባር ማሳየት መቻል አለባቸው ብለዋል።

ሁሉም አካላት ከራ ፍላጎት ይልቅ የሀገርን አስቀድመው ችግሮች በምክክርና በውይይት  እንዲፈቱ በጋራ በመንቀሳቀስና በአበይት ሀገራዊ ጉዳዮች  ከስምምነት ላይ ለመድረስ በሀቅ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

በቡልኮ የጥናት፣ የትምህርትና የሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አብዱልፈታህ አብደላህ በሀገራችን እስከዛሬ ችግሮችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የተሄዱባቸው መንገዶች ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ማስገኘት ካለመቻላቸውም በላይ ያስከተሉብንን ችግሮች በውል መገንዘብ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡

ከዚህም በመነሳት አሁን ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የመፍትሔ አማራጭን መከተል የግድ እንደሚል አመልክተዋል።

እንደ ሀገር ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የሀገርና የዜጎች ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ሁሉ ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል፡፡

አንዱ ወደ ሌላው ከመጠቆም፣ ከእኔነትና የበላይነት መንፈስ በመላቀቅ፣ ከራስ ጥቅም ብቻ ፈላጊዎች የሚመነጭን ኢ-ፍትሃዊ ጥቅም ፈላጊነት ትርክቶች በጸዳ አመለካከት ለብሔራዊ አንድትና ሀገራዊ ሰላም መረጋገጥ የበኩሉን መወጣት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም