ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለትምህርትና ለእውቀት መትጋት አለባቸው – ጅማ ዩኒቨርሲቲ

121

ጅማ ፤ ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ) ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በትምህርታቸው ላይ በማተኮር እውቀት ጨብጠው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም መትጋት እንዳለባቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ።

ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው የትምህርት ዓመት ከ4ሺህ 600 በላይ  አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን ገልጿል፡፡

በተማሪዎቹ የአቀባበል መርሀ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንተ ዶክተር ታደሰ  ሀብታሙ  ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተማሪዎች የመጠቡትን ዓላማ  በመረዳት ለትምህርት ብቻ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በኩል የመማር ማስተማር  ሂደቱን ለማስቀጠል  በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ሁሉም የስራ ክፍሎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎችም በቆይታቸው በትምህርታቸው ላይ በማተኮር   እውቀት ጨብጠው  ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም  መትጋት እንዳለባቸው  ዶክተር ታደሰ  አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቀነኒሳ  ለሚ በበኩላቸው፤ ተማሪዎቻችን የወጡለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ሰላማዊ የመማር ማስተማር አካባቢ እንዲፈጠር የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወደ ዩኒቨርሲቲው ከገቡት መካከል ከወላይታ የመጣው ተማሪ አስራት ካፎ  በሰጠው አስተያየት ፤ “አቀባበሉን ወድጀዋለሁ፣ ጅማ ደስ የምትል ከተማ ናት፣ እዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡

በቆይታውም ጠንክሮ ተምሮ ውጤታማ በመሆን  ቤተሰቡንና ሀገሩን ለመጥቀም  እንደሚጥር ገልጿል፡፡

ከኢሉባቦር የመጣችው ተማሪ አሚና ከማል በበኩሏ፤ የነበረው አቀባበል  በጣም ደስ የሚል ነበር፣ ከተማውም ግቢውም ደስ ይላል፣ አሁን ከኛ የሚጠበቀው ለመጣንለት ዓላማ በሙሉ ትኩረት በመስራት ለስኬት መብቃት ነው” ብላለች፡፡

በስኬት ለማጠናቀቅ ትምህርቷን በትጋት እንደምትከታተል ተናግራለች፡፡