የድሬደዋ አስተዳደር የልማት ፕሮጀክቶችን እያጓተቱ በሚገኙ ተቋራጮች ላይ እርምጃ መውሰድ ሊጀምር ነው

147

ግንቦት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬደዋ አስተዳደር ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ያሳድጋሉ ተብለው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን እያጓተቱ በሚገኙ ተቋራጮች ላይ እርምጃ መውሰድ ሊጀምር እንደሆነ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በአስተዳደሩ የመንገዶች ባለስልጣን በኩል እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገምግሟል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ከንቲባው ከድር ጁሃር እንዳሉት፤  ተቋራጮች በገቡት የስራ ውል መሠረት በጊዜ፣ በበጀት፣ በጥራት ስራቸውን አጠናቀው የማያስረክቡ ከሆነ አስተዳደሩ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይጀምራል።

የልማት ፕሮጀክቶችን በማጓተት እርምጃ የሚወሰድባቸው ተቋራጮች በቀጣይ አስተዳደሩ በሚያወጣቸው ፕሮጀክቶች ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በመሆኑም የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ተቋራጮች በውላቸው መሠረት ፕሮጀክቶችን አጠናቀው አገልግሎት ማስጀመር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ከፕሮጀክት መረጣ እስከ ተቋራጮች ምልምላ ሂደት ውስጥ ያሉ ችግሮች ተፈትሸው የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ተቋሯጮች በገቡት ውል መሠረት እየሰሩ አይደሉም፤ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ ባለመሆኑ በቀጣይ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ናቸው።

ከተቋሯጮቹ የሚቀርቡት ብዙዎቹ ምክንያቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልፀው፤ ለፕሮጀክቶቹ መፋጠን የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ተቋራጮች በበኩላቸው የተነሱ ችግሮችን በአፋጣኝ በመፍታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ሌት ተቀን በመረባረብ በተገባው ውል መሠረት እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል።

አስተዳደሩ ከወሰን ማስከበር ጋር ለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

በድሬደዋ ባለፉት አምስት አመታት የተጀመሩ የአስፋልት፣ የጠጠር፣ የዘመናዊ ድልድዮች፣ በዚህ አመት ደግሞ በዘመናዊ መንገድ ዋና ዋና የእግረኛ መንገዶችን የመገንባት ተግባራት እያከናወነ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የተጓተቱ መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል።