የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ለሰባት መምህራን የአካዳሚክ ማዕረግ እድገት ሰጠ

113

ሰመራ፤ ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ)፡ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ለሰባት የዩኒቨርሲቲው መምህራን የአካዳሚክ ማዕረግ እድገት መስጠቱን አስታወቀ።

በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው በ2014 የትምህርት ዘመን አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁንም ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አብዱልፈታህ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤    ለሰባት መምህራን የአካዳሚክ ማዕረግ እድገት የተሰጠው የተቋሙ ሴኔት ግንቦት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ነው።

በታወቁ የጥናትና ምርምር ጆርናሎች ላይ የምርምር ስራቸውን ላሳተሙና በመማር ማስተማር ስራው ያከናወኑትን ውጤታማ ስራ መነሻ በማድረግ ለአምስት መምህራን የረዳት ፕሮፌሰርነት፤  ለሁለት መምህራን ደግሞ የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
 በዚህም አባይ ወዳይ፣ ኩሴ ኡርማሌ ፣ እፀይ ወልዱና ኡስማን አህመድና  ሰጥዬ አበባው የረዳት ፕሮፌሰርነት፤ ለዶክተር ተሻገር ዱቤና ለዶክተር ህሉፍ ነጋሽ ደግሞ የተባባሪ ፕሮፌሰር ማዕረግ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ3 ሺህ 500 በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን   አቶ አብዱልፈታህ ጨምረው ገልጸዋል።

አዲስ ገቢ ተማሪዎችን የሚቀበሉት   ግንቦት 13 እና 14/ 2014ዓ.ም መሆኑን አስታውቀዋል።።

ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማህበረሰብና ጋር ተቀራርቦ በመስራት ከዚህ በፊት የሚታወቅበትን የሰላማዊ መማር ማስተማር እንቅስቃሴውን  ጠብቆ በማስቀጠል ከቅበላ ጀምሮ ተማሪዎች በተቋሙ ቆይታቸው ያለምንም ችግር  በመልካም ሁኔታ ትምህርታቸውን ተረጋግተው መከታተል እንዲችሉ የቅድመ-ዝግጅት ስራ መከናወኑን  ጠቁመዋል።