በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው

202

ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ ) በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ከፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩ በዋናነት መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መፍታት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶች ውስጥ በአገር ውስጥ ምርት የምትሸፍነው እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚሆነውን መድኃኒት እና የሕክምና ግብዓቶችን ከውጭ እንደምታስገባም ነው የገለጹት፡፡

መንግሥት በአሥር ዓመቱ የስትራቴጂክ አቅድ ውስጥ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን አንስተው፤ በዚህም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 60 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒትና የሕክምና ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ጨምሮ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል እና ሕክምና አቅርቦት አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት አለመኖር የዘርፉ ዋነኞቹ ማነቆዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የአገሪቱን የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች ፍላጎት በማሟላት ረገድ በሚፈለገው ደረጃ እየሰሩ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

ችግሮቹን መቅረፍ ከተቻለ የዘርፉ አምራቾች የኢትዮጵያን ፍላጎት እስከ 40 በመቶ መሸፈን እንደሚችሉም  አስገንዝበዋል፡፡ 

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በ1962 ዓ.ም የኖርዌይና ሲዊድን የህጻናት አድን ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የስጋ ደዌ በሽታን በጥልቀት ለመረዳትና የመከላከያ ክትባት ለመሥራት የሚረዱ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለማጠናከር የተቋቋመ ነው፡፡

ተቋሙ በ2008 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተደራጀ ሲሆን፤ በዚህም አሁን ላይ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለትግበራ የቀረቡ የሕክምና ሙከራዎችን በአገር ደረጃ የማሳደግ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም