ተቋማት ለአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት ድጋፍ በማድረግ ትውልዱን በእውቀት ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል

112

ግንቦት 5/2014(ኢዜአ) ተቋማት ለአብርሆት ቤተ-መጽሃፍት ድጋፍ በማድረግ ትውልዱን በሁሉም አይነት እውቀት ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ጥሪ አቀረቡ፡፡
 

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) 10 ሺህ የሚጠጉ መጽሐፍት ለአብርሆት ቤተ -መጽሐፍት አበርክቷል፡

መጽሃፍቱንም  የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ  ዶክተር ሂሩት ካሳው አስረክበዋል፡፡

ኃላፊዋ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ወቅት ተቋማት ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት ድጋፍ በማድረግ ትውልዱን በሁሉም አይነት እውቀት ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢቢሲ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው የንባብ ማዕከላት መስፋፋት የንባብ ባህልን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

የንባብ ማዕከላት ደግሞ በግብዓት ሊሟሉ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢቢሲ በዛሬው እለት 10 ሺህ የሚጠጉ መጽሀፍቶችን ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት እንዳበረከተ  ገልጸው ፤መጽሀፍቶቹም ከሰራተኛውና ከኢቢሲ አጋር ተቋማት የተሰበሰቡ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኢቢሲ በቀጣይም የተለያዩ መጽሐፍትን በማሰባሰብ ለቤተ-መጽሃፍቱ ድጋፉ እንደሚያደርግም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተ-መጽሐፍት ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍትን መያዝ የሚችል ሲሆን 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የመጽሃፍት መደርደሪያም አለው።