የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ለተፈናቃይ ወገኖች ምግብ ነክ ድጋፍ አደረገ

138

ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ ) የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ በሸኔ የሽብር ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ምግብ ነክ ድጋፍ አደረገ።

በመማክርት ጉባኤው የጤና ክላስተር አስተባባሪና የቦርድ አባል ፕሮፌሰር ተፈሪ ገደፉ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንዳሉት፤  ድጋፉ በሚኒሶታ አካባቢ ከሚኖሩ ዶክተር ከፍያለ ቦጋለና ወይዘሮ ሰብለ አስናቀ የሚባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን  በማስተባበር የተገኘ ነው።

ድጋፉም ለህፃናት፣ ለነፍሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች ለምግብነት የሚያገለግሉ 100 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና   100 ኩንታል ማካሮኒ መሆኑን ገልጸዋል።

መማከረት ጉባኤው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙና የስነ- ልቦና ጫና ለደረሰባቸው ወገኖች የስነ- ልቦና እና ተያያዥ ህክምና እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፀጋዬ በየነ በበኩላቸው፤ በአሸባሪው ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ከ23 ሺህ በላይ ወገኖች  በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ መጪው ጊዜ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተፈናቃይ ወገኖች ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ድጋፉ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተፈናቃዮች መካከል አቶ ክንፈ የማነ በሰጡት አስትያየት፤ ከ64 ዓመት ባላይ ከኖሩበት ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ተፈናቅለው ለችግር መጋለጣቸውን  ገልጸዋል።

እየተደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው ፤ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመልሳቸው የሚፈልጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም