የተጀመረው የኢንዱስትሪ ንቅናቄ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው

125

ድሬዳዋ ፤ ግንቦት 5/2014(ኢዜአ) ''ኢትዮጵያ ታምርት'' በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የኢንዱስትሪ ንቅናቄ እያስመዘገበ የሚገኘው አበረታች ውጤት መጠናከር እንዳለበት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመለከተ።

በኢንዱስትሪ  ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ የተመራውና የተለያዩ ሴክተሮች አመራሮችን  ያካተተው ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንቅስቃሴን ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለሰነቀችው የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግር ሚና ይኖረዋል ተብሎ የሚታመነውን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በኢንዱስትሪ መንደር የሚገኙ ግዙፍ የመኪና መገጣጠሚያዎችንና አስተዳደሩ ያስገነባቸውን 17 የማምረቻ ኢንዱስትሪ ሼዶች የሥራ እንቅስቃሴም ተገምግሟል፡፡  

ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ በተለይ ለኢዜአ እንዳስረዱት ፤በመላ ሀገሪቱ የተጀመረው የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' የኢንዱስትሪ ንቅናቄ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው፡፡

ከፌዴራል እስከ ክልሎችና ከተሞች ድረስ ዘርፉን የሚመሩትና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ያደረጉት ጥረት እንቅስቃሴ ይጠናከራል ብለዋል፡፡

በንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ በቦታ፣ በጥሬ ዕቃዎች፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ በውጭ ምንዛሪና የመሳሰሉ ችግሮች ተዘግተው ከነበሩት 428 ኢንዱስትሪዎች 128ቱ በተደረገላቸው ድጋፍ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የተቀሩት ሥራ ለማስጀመርም የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ንቅናቄው ተከትሎ በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው ድጋፍ የተዘጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው፡፡

''በድሬዳዋ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ተግባራት ማጠናከር ይገባል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተቀየሰው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን በማሳካት ሀገሪቱ ከግንባር ቀደሞች መካከል አንዷ ያደርጋታል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ድሬዳዋ ከጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ፣ ከወደቡ ጋር በዘመናዊ ባቡርና የየብስ ትራንስፖርት መተሳሰሯና የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የደረቅ ወደብ ባለቤት መሆኗ፣  ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባቱ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በኢንዱስትሪ መንደር የተገነቡት ሼዶችና ሁሉን አቀፍ የኢንዱስትሪ ንቅናቄ የምጣኔ ሃብት መሠረቱን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እንደሚረዱ አብራርተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው፤ በአስተዳደሩ የኢንዱስትሪ ንቅናቄና የተቀናጀ ድጋፍ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ችግሮች የተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ምርት መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሚገኙ 370 ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን  አስታውቀዋል።

የቡድኑ ጉብኝት  በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች በመድፈን የተሻለ ሥራ ለማከናወን እንደሚያግዝ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከዓመታዊ ጠቅላላ ምርት /ጂዲፒ/ አሁን ካለበት   5 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ለማድረግ፣ ምርቱንም ከ30 ወደ 60 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

በዘርፉ ለ5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ከውጭ ምንዛሪ የሚገኘውን ገቢ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለማድረስ መታቀዱን መረጃው ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም