የሶማሌና አፋር ክልሎች ህዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው- የሰላም ሚኒስቴር

96

ጂግጅጋ ፤ ግንቦት 5/2014(ኢዜአ) "በምንም መንገድ የማይለያየውን የሶማሌና አፋር ክልሎች ህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም ገለጹ።

በጂግጅጋ ከተማ በተዘጋጀው  የአፋርና ሶማሌ ክልሎች የሰላምና የልማት ምክክር መድረክ ላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ ክልሎች  ያጋጠመውን ችግር  ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ ተቋቋሞ እየተሰራ ነው።

የጋራ ኮሚቴው በሁለቱ ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የተወጣጡ አካላት የተካተቱበት መሆኑን አመልክተዋል።

"በምንም መንገድ የማይለያየውን የሶማሌና አፋር ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የህዝቦችን  ሰላምና ደህንነት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲጠበቅ ለማድረግ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል አርብቶ አደር አካባቢ የተከሰተው ድርቅ በተለያዩ አካላት በተደረገው ርብርብ የተፈራውን አደጋ ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

የክልሉ መንግስት በሰጠው አመራር እና መላው ህዝብ  በተለይ የሶማሌ ማህበረሰብ የእርስ በእርስ መረዳዳት የቆዩ ባህሉ ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቋቋም መቻሉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ሚኒስትሩ ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የምስራቅ ዕዝ መከላከያ አመራሮችና የፖሊስ መኮንኖች በፋፈን ወንዝ ዳሪቻ በ30 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለውን የፍራፍሬና አትክልት እርሻ እየጎበኙ መሆናቸውን ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም