በምዕራብ ሸዋ ሰባት የውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቁ

136
አምቦ ግንቦት 10/ 2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አምስት ወራት ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሰባት የንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ከ32 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ተጠቃሚ ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡ የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሾ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶቹ ባለፈው ዓመት መንግስትና አጋር የልማት ደርጅቶች በመደቡት 39 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ ከነበሩ 47 ፕሮጀክቶች መካከል ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው ኖኖ፣ ዳኖ ፣ ሜታ ሮቢ፣ ሚዳ ቀኝና አምቦ ወረዳዎች እንደሆኑ ተመልክቷል። የውሃ ፕሮጀክቶቹ ከጥልቅ የውሃ ጉርጓድ ቁፋሩ የተገነቡ ሲሆን ወደ ተጠቃሚው የሚያደርሱ የቧንቧ ዝርጋት፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችና የማከፋፊያ ቦኖች ያካተቱ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ለአገልግሎት የበቁት  የውሃ ፕሮጀክቶች የዞኑ አጠቃላይ የገጠር ንፁህ መጠጥ ውሀ ሽፋን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 58 በመቶ ወደ 60 በመቶ ከፍ እንዲል አስችለዋል። ግንባታቸው   ከ65 እስከ 85 በመቶ የደረሱት ቀሪዎቹ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችም  በተያዘው  ዓመት መጨረሻ ሲጠናቀቁ ሽፍኑን ወደ 70 በመቶ እንደሚያደርሰው  ይጠበቃል። በኖኖ ወረዳ የመቱ ስላሴ ቀበሌ አርሶአደር  ነገሪ ሙሊሳ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በእግር ስድስት  ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓዝ ጨለለቂ  ከተባለ ወራጅ ወንዝ ውሃ በመቅዳት ሲጠቀሙ መቆየታቸውን  አስታውሰዋል ። " ወንዙ ለእንስሳት ንክኪና ለተለያዩ ቆሻሻ  የተጋለጠ በመሆኑ ከነቤተሰቤ የውሃ ወለድ በሽታ ያጋጥመን ነበር" ብለዋል ። በቅርቡ በአካባቢያቸው የተመቻቸላቸው የንጽሁ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የነበረባቸውን  ችግር እንዳቃለላቸው አመልክተዋል። " ንጹህ የመጠጥ ውሃ በመጠቀማችን ተደስተናል " ያሉት ደግሞ በአምቦ ወረዳ የቂባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጫልቱ መገርሳ  ናቸው ፡፡ በቀበሌያቸው በተገነባው የውሀ ተቋም ከዚህ ቀደም ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሀ ከወንዝ ለመቅዳት የሚያባክኑት ጉልበትና ጊዜ ቆጥበው ለሌላ ስራ ማዋል እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል፡፡ የሚዳ ቀኝ ወረዳ አርሶአደር  መገርሳ ጉሊቲ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን  በመጀመራቸው የነበረባቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦች ችግር መቃለሉን ገልጸዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የተገነቡት የውሃ ተቋማት በእንክብካቤ እንደሚጠቀሙባቸውም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም