በፈንታሌ ወረዳ 40 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው

105

ግንቦት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ የመስኖ ልማት ስራዎችን ጨምሮ 40 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተተገበረ እንደሆነ ተገለጸ።

ከፑንትላንድ የመጣ ልዑክ በአካባቢው እየተካሄደ ካለው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትግበራን ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል ጉብኝት እያካሄደ ይገኛል።

በወረዳው በፕሮጀክቱ የተሰሩ ስራዎች እና የተገኙ ውጤቶች ላይ ለልዑኩ ገለጻ ተደርጓል።

በቆላማ አካባቢዎች ፕሮጀክት የምስራቅ ሸዋ ዞን እና ምዕራብ ሀረርጌ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ወርቁ ጋዲሳ እንዳሉት፤ በፕሮጀክቱ በሶስት ወረዳዎች ላይ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የእንስሳት ህክምና ማዕከልና የጤና ኬላ ግንባታ እየተከናወነ ነው።

የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም ማድረግና የመስኖ ልማት ላት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአካባቢዎቹ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገው እንቅስቃሴም የቁጠባና ብድር ማህበራት እንዲጠናከሩ መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይም የመስኖ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በስራ ዕድል ፈጠራ በኩል ውጤታማ እንቅስቃሴ መደረጉን ጠቅሰው፤ በፕሮጀክቱ 40 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ የአርብቶ አደር አኗኗር ጥናት ዳይሬክተር አቶ ከተማ ዑርጌ በበኩላቸው በክልሉ ድርቅን ለመቋቋም እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በ217 ሄክታር መሬት ላይ በአጭር ጊዜ የሚደርስ የእንስሳት መኖ ልማት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ