የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ወላፈን

310

በሕዳር 1917 ዓ.ም ሩሲያን ለሶስት ክፍለ ዘመናት እየተፈራረቁ የመሯት የ’ሮማኖቭ’ ንጉሳዊ ስርወ መንግስት ቤተሰቦች የገዢነት ዘመን አበቃ። ቭላድሚር ሌኒን የሚመራው አክራሪው ሶሻሊስት ፓርቲ 'ቦልሼቪክ' በትረ ስልጣኑን ተረከበ። የገዢነት ስልጣኑን የተረከቡት ቦልሼቪኮች በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የኮሚኒስት መንግሥት በሩሲያ አቋቋሙ። አብዮተኛው የቦልሼቪክ መንግስት ብዙም ሳይቆይ ሩሲያውያን ወደ ዕርስ በርስ ጦርነት ገቡ። ‘ቀይ’ና ‘ነጭ’ ጦር ተብለው የሚጠሩ አንጃዎች ጎራ ለይተው ደም አፋሳሽ ፍልሚያ አደረጉ። ቀዩ ጦር የቭላድሚር ሌኒንን ቦልሼቪክ መንግስት የሚወክል ሲሆን ነጩ ጦር ደግሞ የንጉሳዊ ስርዓቱ ጠበቃ ሆኖ ቀረበ። በመጨረሻም ቦልሼቪኮች አሸናፊ ሆነው ወጡ።

በ1923 ዓ.ም የሌኒን ቀዩ ጦር ድል ማግኘቱን ተከትሎ ሶቪየት ሕብረት ተመሰረተ። ሶቪየት ሕብረት በሩሲያ የበላይነት የሚመራውና 15 ራስ ገዝ አስተዳደሮችን አቅፎ ከዓለማችን እጅግ ኃያላን እና ተደማጭነት ካላቸው መንግሥታት አንዱ ሆኖ ወጣ። ሕብረቱ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ ቤላሩስ፣ ኡዝቤኪስታን፣ አርሜኒያ፣ አዘርባጃን፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ሞልዶቫ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ታጂኪስታን፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዌኒያ እና ኢስቶኒያ ያቀፈ ነበር። ሶቪየት ሕብረት ከ290 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የነበረውና ከ100 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ነበር። ሁኔታው ሕብረቱን በዓለም እንደ ኃያል መንግስት ያስቆጠረና በቀዝቃዛው ጦርነት ከአሜሪካ ጋር ተቀናቃኝነታቸው ጎልቶ የታየበት ጊዜም ነበር። በወቅቱ ሶቭየት ሕብረት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ባለቤትና በምስራቅ አውሮፓ አንደ ‘ዋርሶዎ’ ያለ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጥምረትን ጭምር መስርቷል።

በ1948 ዓ.ም ሶቪየት ሕብረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከናዚ ጀርመን ቁጥጥር ነጻ በወጡ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት የኮሙኒስት ስርዓተ ማሕበር ደጋፊ መንግስታትን ዘረጋ። ሆኖም አሜሪካና እና እንግሊዝ የኮሙኒዝም ወደ ምዕራብ አውሮፓ እና ወደ ሌላው የዓለም ክፍል መስፋፋት አላስደሰታቸውም ነበር። ነገሮች በዚህ ሁኔታ እያሉ በ1949 ዓ.ም አሜሪካ፣ ካናዳ እና የአውሮፓ አጋሮቻቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን መሰረቱ። የምዕራቡ ዓለም አገሮች የመሰረቱት ጥምረት በሶቭየት ሕብረት እና በተባባሪዎቻቸው በጎ ምልከታ አልተሰጠውም። በአንጻሩ ለ’ኔቶ’ ምላሽ ይሆን ዘንድ በ1955 ዓ.ም ሶቭየት ሕብረት የዋርሶ ስምምነት የተባለ ጥምረት አጠናከረች።

የቀዝቃዛው ጦርነት ውቅት የኃያላን የበላይነት ሽኩቻ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በፕሮፓጋንዳ ግንባሮች በምስራቅ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ጠንክሮ ይካሄድ ነበር። በመጨረሻም በሁለተኛው የዓልም ጦርነት ማብቂያ አካባቢ የጀመሩትና በቀጥቃዛው ጠርነት የጠነከሩት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በ1991 ሶቭየት ህብረትን ለውድቀት ዳረጓት። የጆሴፍ ስታንሊን አስተዳደር ሶቭየት ሕብረትን በመበተን ሒደት ውስጥ ትልቅ ድርሻም ነበረው። ሕብረቱ በ1991 ዓ.ም በህዝበ ውሳኔ እንዲፈርስ ተደረገ። በ1993 ዓ.ም ሩሲያ በፌዴሬሽንነት ተዋቀረች። ከዛ ወዲህ የሩሲያና የምዕራቡ ዓለም ግንኙነት የሰመረ ሊሆን አልቻለም።

ሩሲያ እና ዩክሬን

የሶቪዬት ሕብረት ከመፍረሱ ቀደም ብሎ ዩክሬን በ1991 ዓ.ም ሯሷን የቻለች ነፃ ሀገር መሆኗን አወጀች። ይህን ውሳኔ ተከትሎ በሩሲያና ዩክሬን መካከል አለመግባባቶች ቢፈጠሩም ጠንከር ያለ አለመግባባት ጐልቶ መታየት የጀመረው እአአ በ2014 ገደማ ነው። በወቅቱ በዩክሬን የተነሳው የ’ብርቱካናማ’ አብዮት ዋናው የአገራቱ አለመግባባት ምንስኤ አንደሆነም በስፋት ይጠቀሳል። የአብዮቱ መነሻ ከሞስኮ ድጋፍ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው የወቅቱ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የነበራቸውን የንግድ ስምምነት ለመሻር ያሳለፉት ውሳኔ ህዝባዊ አመጽ መቀስቀሱ ነው። በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ በ2014 ዓ.ም ከስልጣናቸው እንዲወገዱና አፍቃሪ ምዕራብዓዊ የሆነ መንግስት በዩክሬን እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። ብርቱካናማ አብዮት በምዕራብዊያን ፍላጎት አቅጣጫ መመራቱ የተንጸባረቀበትና በ'ሞስኮ'ና በ'ኬይቭ' መካከል ውጥረቱ እንዲባባስ ያደረገ ነበር።

በዩክሬን አፍቃሪ ምዕራብዓዊ መንግስት መምጣት ያሳሰባቸው የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካን እና የአውሮፓ ሕብረትን “የፋሺስት መፈንቅለ መንግስት” አድርገዋል ሲሉ ከሰሷቸው። ከዚህም አልፎ ሩሲያ ከዩክሬይን ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችውን ክሬሚያን ወደ ሩሲያ እንድትካለል አደረጉ። በሩሲያ በኩል የተወሰደው እርምጃ በሩሲያና በዩክሬን መካከል የነበረውን ግንኙነት የበለጠ ከማሻከሩ አልፎ ከምዕራባውያን ጋር ትንቅንቁ ጠንክሮ ቀጠለ። አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን ቢያስከትሉም ሩሲያ ክሪሚያን በመያዝ በጥቁር ባህር የባህር ኃይል ጣቢያን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ቻለች።

ቀጥሎም በምስራቃዊ ዩክሬን ዶንባስ ግዛት ውስጥ ያሉ ሁለት ራስ ገዞች በሩሲያ እንደሚደገፉ ፍንጭ ሰጡ። እነዚህ በሩስያ የሚደገፉትና በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚገኙት የዶንቦስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ (DPR) እና የሉጋንስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ (LPR) አካባቢውን ለመቆጣጠር ከመንግስት ጦር ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ። "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" እንዲሉ እነዚህ ክስተቶች በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት እንዲነግስ የመጀመሪያ ምልክት ሆኑ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ዩክሬን ያቀረበችው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነት ጉዳይ ለሩሲያ ትልቅ የራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል። ሩሲያ የዩክሬን የኔቶ አባል መሆን ለጥቃት ያጋልጠኛል ስትል ስጋቷን ከፍ አድረጋ ገለጸች።

በመጨረሻም ሩሲያ ሕግ ማስከበር ባለችው ዘመቻ የካቲት 24 ቀን 2022 ዓ.ም ወደ ዩክሬን ድንበር ዘልቃ ጥቃት ፈፀመች። በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ድንበር ተሻግሮ አሜሪካና የተቀሩት ምዕራባውያን ሀገራት ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው ሩሲያን እንዲያወግዙ አድርጓቸዋል። የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ምዕራባውያን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ በመጣል ላይ ናቸው። የጦርነቱ የተጽእኖ በትር ግን ከማእቀብ ጣዮቹ ሀያላን እስከ ደሀዎቹ የአፍሪካ አገራት ማረፉ አልቀረም።

በዓለም ገበያ ከሚሸጠው ስንዴ 30 በመቶ ድርሻ ያላቸው ዩክሬንና ሩሲያ ናቸው። ሁለቱ አገራት በበቆሎና የሱፍ አበባ ዘይት ግብይት ሚናቸው የላቀ በመሆኑ አሁን ለሚታየው የዋጋ ግሽበት ድርሻቸው ትልቅ እንደሆነ አይካድም። ስንዴና መሰል የእህል አይነቶች ዋጋ ማሻቀብ የምግብ ዋጋ መረጋጋትን እያወከ ይገኛል።  

ዳፋው ለዓመል አቀፍ ተቋማትም ተርፏል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ "ጦርነቱ የሁለቱ ሀገራት ቀውስ ብቻ አይደለም። ቀውሱ በምግብ ሸቀጦች የአቅርቦት ሰንሰለት እና ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል" ብለዋል፡፡ ከጦርነቱ በፊት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከሚያስፈልገው ስንዴ 50 በመቶውን ከዩክሬን ይሸምት እንደነበርም አንስተዋል። "በተከሰተው ቀውስ የታየው የዋጋ ጭማሪ ድርጅቱን በወር ከ60 እስከ 75 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስወጣ አስታውቀዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በአለም ላይ የተከሰተው የምግብና ነዳጅ ዋጋ መጨመር በአንዳንድ ሀገራት ላይ አለመረጋጋት እንዳያስከትል ስጋት የጫረ ሲሆን በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ደቡብ አሜሪካ፣ መካከለኛው እስያና መካከለኛው ምስራቅ የዚህ ስጋት ሰለባ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ሀገራቱ የገቡበት ጦርነት የአለምን ኢኮኖሚና ጂኦፖለቲካ በእጅጉ  የፈተነው ሲሆን የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት አቅጣጫና የሸቀጦች አቅርቦት ትስስር እንዲለወጥም ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም አለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ ትኩሳትን በመፍጠር ኢኮኖሚውን ወደማሽመድመድ እንዳያደርሰው ተሰግቷል፡፡

የጦርነቱ ተጽእኖ በአውሮፓ

የችግሩ ነበልባል የጦርነቱ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ የሆነችውን ዩክሬንን ከሁሉ በፊት ቢገርፋትም በሩሲያ ላይ የተጣለው የፋይናንስ ማዕቀብ የገንዘብ ዝውውሩንና ንግዱን በመጉዳት የሸቀጦች ዋጋ እንዲያሻቅብ ምከንያት ሆኗል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚ ጠንካራ በሆነችው ሩሲያ መገበያያ ገንዘብ ሩብል ላይ የተከሰተው የዋጋ ማሽቆልቆል በሀገሪቱ ግሽበትን አስከትሏል፡፡

የአውሮፓ ሀገራትመ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት እያስመዘገቡ ነው። ሀገራቱ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ አይተውት የማያውቁት የዋጋ ግሽበት ነው እያስመዘገቡ ያሉት። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዩሮዞን ሀገራት በ30 እና 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡን መረጃ መለዋወጣችን አይዘነጋም። ለዚህ የዋጋ ግሽበት መባባስ ዛሬም ድረስ መፍትሄ ያልተገኘለትና ዓለም በጠቅላላ ያናጋው የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ነው።

በቼክ በሚያዝያ ወር ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 14.2% ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከ1993 ወዲህ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ነው። እንዲሁ በዴንማርክ አመታዊ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ወር ወደ 6.7 % የጨመረ ሲሆን ይህም ከ1984 ወዲህ  ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት ነው። በግሪክ በሚያዝያ ወር 10.2 በመቶ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ተመዝግቧል፤ ይህም ከ1995 ወዲህ ከፍተኛው ነው።

ሩሲያ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበው ነዳጅ መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ የተፈጠረው መስተጓጎል በርካታ ሀገራትን ፈተና ላይ ጥሏቸዋል፡፡ይህ ተግዳሮት ደግሞ ከኮቪድ ወረርሽኝ ለማገገም የሚታገሉ የአውሮፓ ሀገራትን ወደ ባሰ አዘቅት እንዳይከታቸው አስግቷል፡፡ አሁን ላይ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት የፋይናስ ወጪያቸው እያሻቀበ የመጣ ሲሆን በተጨማሪም በስደተኞች በመጥለቅለቃቸው ያልተገባ ጫና አድሮባቸዋል፡፡ ከዩክሬን የተሰደዱ 3 ሚሊዮን ሰዎችም የተጠለሉት በነዚህ ሀገራት ውስጥ መሆኑ በራሱ ኢኮኖሚያቸውን ፈትኖታል፡፡

የአውሮፓ ሀገራት ጦርነቱን ተከትሎ ለነዳጅ፣ ለደህንነትና ለመከላከያ የሚያወጡት ገንዘብ በመጨመሩ በአመታዊ በጀታቸው ላይ ጫና አሳድሮባቸዋል፡፡ በተጨማሪ በርካታ ሀገራት የሩሲያን ሀብት ለማገድ  የጀመሩት እንቅስቃሴ በማገገም ላይ የሚገኘውን የአለም ገበያ  የሚጎዳው ሲሆን ባለሃብቶችም ሀብታቸውን ከማፍሰስ እንዲቆጠቡ አስገድዷቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በርካታ የአውሮፓ ባንኮች ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ውጥረቱ በቀጣይ ግንኙነታቸው ላይ መጥፎ ጥላ አሳርፏል፡፡

አሜሪካ

ችግሩ በደሃ አገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ማዕቀብ በሩሲየ ላይ እንዲጣል ምዕራባውያን አገሮችን በምታስተባብረው አሜሪካም እየተስተዋለ ነው፡፡ አሜሪካ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላት ትሰስር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ተከትሎ ጫናው በቀጥታ ባይንካትም አሁን ላይ የተመዘገበባት የዋጋ ግሽበት ከ 40 አመት በኋላ ከፍተኛው ሆኗል፡፡

ኒውዮርክ ፖስት የኢኮኖሚ ባለሙያውን መሐመድ ኤል ኢሪያን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በአሜሪካ የዋጋ ግሽበት በበጋው በሦስት እጥፍ የሚያድግ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካውያን ላይ የገንዘብ ቀውስን ያስከትላል ብሏል፡፡ ጦርነቱ በዕቃዎች ዋጋ፣ አቅርቦት ሰንሰለትና መጓጓዣ ላይ የሚያሳርፈውን መስተጓጎል  ተከትሎ የሚከሰተው የኑሮ ውድነት አሜሪካውያን የሚሰማቸው በበጋው ወቅት ላይ ነው ይላሉ፡፡ የግምጃ ቤት ሴክሬታሪዋ ጃኔት የለን በበኩላቸው፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በዓለም ከፍተኛ ውጥንቅጥ በመፍጠር ኢኮኖሚውን ይጎዳል በአጠቃላይ በአሜሪካም የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል ብለዋል፡፡

መካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ

በነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የምግብና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መከሰቱ ህዝባቸውን ፈተና ላይ እንደሚጥለው የማያጠያይቅ ሲሆን ጠበቅ ያለው አለም አቀፍ የፋይናንስ ዝውውር ተጨማሪ ፈተና እንደሆነባቸው እየታየ ነው፡፡

ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ የገበያዎቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚሸምቱት ጥራጥሬ ላይ ጥገኛ ናቸው። ግብጽ ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ጥራጥሬ 60 በመቶው ከሩሲያ እና የዩክሬን የሚገዛ ነው። ይኸ በቱኒዚያ 46 በመቶ፣ በሞሮኮ ደግሞ 17 በመቶ ይደርሳል። የኤኮኖሚ ተንታኟ ካሊ ዴቪስ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ "ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚያስገቡት ጥራጥሬ ላይ ጥገኛ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የአገራቸውን የጥራጥሬ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስፈልጋቸውን ምርት ለማግኘት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት ዳቦን ጨምሮ የሚያስፈልጓቸውን የምግብ አይነቶች ለማሟላት እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል" ሲሉ ይናገራሉ። ስንዴን በብዛት ከዩክሬንና ሩሲያ የምታስገባው ግብፅ ከአሁኑ በዳቦ ዋጋ ውድነት እየተሸበረች ሲሆን፣ አልጄሪያም በዋጋ ንረቱ ቀዳሚ ተፈታኝ ሆናለች፡፡

ለምሳሌ ግብጽ 80 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍጆታዋን ከሩሲያና ዩክሬን የምታስገባ መሆኗን ተከትሎ ችግሮች እየፈተኗት ነው፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎቿም ጎብኚዎች በመቀነሳቸው ከፍተኛ የሚባል ገቢ እያሳጣት ነው፡፡ የዋጋ ግሽበትና የመንግስት ወጪ መናር ደካማ የሆነውን የሀገራቱን አመታዊ ዕቅድ ያስተጓጉለዋል፡፡

ግብጽ የዳቦ ድጎማ በማቆሟ በርካታ ተቃውሞዎች መነሳታቸው የሚታወስ ሲሆን የአሁኑ ቀውስ ታክሎበት ሀገሪቱን ፈተና ውስጥ ከቷታል፡፡ በሞሮኮም የነዳጅ ዋጋ መጨመርን በመቃወም የአገሪቱ ሰላማዊ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል። የሩሲያና ዩክሬን ግጭት በሀገራቱ ያሉትን ቀውሶች በማባባስ ተጨማሪ ፖለቲካዊ አደጋ ያስከትላል በማለት ተንታኞች ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

በተጨማሪም በአለም ላይ የተከሰተው አስከፊ የፋይናንስ ቀውስ የካፒታል ፍሰቱን በመገደብ ሀገራቱ ብድር የሚያገኙበትን ቀዳዳ በመዝጋት የፋይናስ ፍላጎታቸው የናረ እንዲሆን ያስገድዳቸዋል፡፡ የዋጋ ማሻቀብ በተለይ የማህበራዊ ደህንነት ማበረታቻ ወይም ሴፍቲ ኔት ደካማ የሆነባቸውንና ጥቂት የስራ ዕድል የሚፈጥሩና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን መንግስታት ለከፍተኛ አለመረጋጋትና ማህበራዊ ቀውስ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት

አካባቢው የኮቪድ ወረርሽኝ ካደረሰበት ተጽአኖ ቀስ በቀስ እያገገመ ባለበት በዚህ ወቅት ይህ ቀውስ መከሰቱ በእሳት ላይ ጭድ ሆነበታል፡፡ በርካታ የአካባቢው ሀገራት በውስጥ ግጭት የሚታመሱ መሆናቸውን ተከትሎ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተፈጠረው ግጭት የነዳጅንና የምግብን ዋጋ በከፍተኛ መጠን በማናር ጉዳት ላይ ጥሏቸዋል፡፡

በግጭቱ የአንዳንድ ሀገራት የጀርባ አጥንት የሆነው ቱሪዝም ክፉኛ የተጎዳ ሲሆን አለም አቀፉን ገበያን ሰብረው በመግባት ለመወዳደር አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ በርካታ የአካባቢው ሀገራት የደረሰባቸውን ቀውስ የሚከላከሉበት ፖሊሲ የሌላቸው በመሆኑ የተጋረጠባቸውን ስጋት ለመቀልበስ አቅም አጥተዋል፡፡

ይህ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በማሳደር ፣የመንግስትን የዕዳ ጫና ከፍ በማድረግ ከኮቪድ ወረርሽኝ ያላገገመውን ኢኮኖሚና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለተጨማሪ መከራ ይዳርጋቸዋል፡፡

በማይታመን መጠን ጭማሪ ያሳየው የስንዴ ዋጋ አፍሪካን እየፈተናት ሲሆን የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡን ተከትሎ የህዝቡ ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እየወረደ መሆኑን አመላካቾች እያሳዩ መጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያም ከ 200 በመቶ በላይ ጭማሪ ያሳየው የማዳባሪያ ዋጋ 4 ሺ 800 ብር መድረሱ በግብርና ዘርፉ ምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ የዋጋ ንረቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡

የምዕራብ ንፍቀ ክበብ

የምግብና የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ አካባቢውን እያመሰው ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ታክለውበት ቀጠናው ስጋት ላይ ወድቋል፡፡ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው የሸቀጦች ዋጋ ላቲን አሜሪካንና የካሪቢያን ሀገራትን ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የዳረጋቸው ሲሆን ወቅታዊ ግሽበቱ ከ 8 በመቶ ማለፉ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ብራዚል፣ሜክሲኮ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ እና ፔሩ ጉዳቱ ያረፈባቸው ቀዳሚ ሀገራት ናቸው፡፡

የእድገት ግስጋሴአቸው መገታቱና የሸቀጦች እና የነዳጅ ዋጋ መናሩ መካከለኛው አሜሪካንና የካሪቢያን ሀገራትን አስመጪዎች ፈትኗቸዋል፡፡ በአንጻሩ ዘይት፣ መዳብ፣ ብረትና የሰብል ምርቶችና የሚልኩ ሀገራት በመጠኑም ቢሆን ጫናውን ለመቋቋም አቅም ሆኗቸዋል፡፡ የደረሰባቸው የገንዘብ ቀውስ መጠነኛ ቢሆንም ጦርነቱ ተፋፍሞ ከቀጠለ ግን አለም አቀፉ የፋይናንስ ሰርዓት ስለሚጎዳ እነሱም የገፈቱ ቀማሽ መሆናቸው አይቀርም፡፡

የእስያና ፓስፊክ ሀገራት

እነዚህ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተገደበ መሆኑ ጫናው በቀጥታ እንዳይነካቸው ቢያደርጋቸውም በአውሮፓና በአለም ኢኮኖሚ ላይ ያለው እድገት መቀዛቀዝ ከፍተኛ ምርት የሚልኩ ሀገራትን መጉዳቱ አይቀርም፡፡ በግጭቱ መጠነ ሰፊ ጉዳት እየደረሰባቸው ከሚገኙ የእስያ ሀገራት መካከል በከፍተኛ መጠን ነዳጅ ወደ ሀገራቸው የሚያስገቡት ህንድና የተወሰኑ የፓስፊክ ደሴቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይም በሩሲያ ጎብኚዎች የሚዘወተሩ የቱሪስት መዳረሻ ያላቸው ሀገራት ቀውሱ ፈትኗቸዋል፡፡ ቻይና በቀጥታ የሚደርስባት ጉዳት ባይኖርም የሸቀጦች ዋጋ መናርና የፍላጎት መቀዛቀዝ ፈተና ሊሆኑባት ይችላሉ፡፡

ጃፓንና ኮሪያም የሚደርስባቸው ጫና እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም አሁን ላይ በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርጉት ድጎማ ማጨመሩ ቀውሱን ያለ ስጋት እንዲያልፉ ሊረዳቸው ይችላል፡፡

ከፍተኛ የሆነው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ህንድን ለከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ዳርጓታል፡፡ በእስያ ያለው የምግብ ዋጋ ጫና በሀገር ውስጥ አምራቾች ምርት መሸፈኑ ስጋቱን ያቀለለው ሲሆን በተለይም ሀገራቱ የሩዝ ተጠቃሚ መሆናቸው ከስንዴ ጥገኝነት አላቋቸዋል፡፡

ነገር ግን የምግብ ዋጋ መናርና የነዳጅ ዋጋ መናር የሸቀጦችን ዋጋ ሊያንረው ይችላል፡፡ ይህን ለመከላከል የሚያደርጉት ድጎማ እንዲሁም በነዳጅ ፣ምግብና ማዳበሪያ መሸጫ ዋጋ ላይ ጣራ ማስቀመጣቸው ቅጽበታዊ የሆነውን ጫና ለመቋቋም ያግዛቸዋል፡፡

መውጫ መንገድ

በዙዎች ጦርነት መቼ እንደሚጀመር እንጂ መቼና እንዴት እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም የላሉ። ዓለምን እያጋጠመ ላለው የኢኮኖሚ መንገዳገድ ዋንኛው መውጫ መንገድ የጦርነቱ መቋጨት ቢሆንም መቼ የሚለው ግን ዛሬም መልስ የለውም። በመሆኑም አገሮች የራሳቸውን ስልት እየቀየሱ የሚደርስባቸውን ጫና ለማቃለል እየተጉ ነው። ኢትዮጵያም ከጦርነቱ ቀጠና በሺሕ ማይሎች ብትርቅም ቀውሱ ከሚያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ማምለጥ አልቻለችም፤ አትችልምም፡፡ የተጽእኖውን በትር ለመቋቋም የሚያስችል ስልት ቀይሶ መስራት ግን ትክክለኛው መውጫ መንገድ ይሆናል።

ኦክስፎርድ ኤኮኖሚክስ በተባለ ተቋም ተንታኝ የሆኑት ካሊ ዴቪስ እንደሚሉት ከውጭ በሚያስገቡት ስንዴ ዜጎቻቸውን የሚመግቡ አገሮች የግዢ ስንዴ ላይ ያለውን ጥገኝነት በቀላሉ መየት የለባቸውም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ የጀመረችው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በከፍተኛ ደረጃ እየጠቀማት ይገኛል። ይህንን አጠናክሮና አስፍቶ መምራትና መስራት ያሻል።

መሰረታዊ የሆነ የአኗኗር ባህርይ ለውጥ ማምጣት ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ቀዳሚ  የሆነውን የምግብ ዋስትና ጥያቄ መመለስ የሚቻለው የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ በማምጣት ነው። በምግብ ዙሪያ እየሰሩ ያሉ በርካታ ድርጅቶች ከሚያነሷቸው ሃሳቦች መካከል ዋነኛው ምግብን በተመለከተ የተራራቀውን የሰዎች አመለካከት መቀየርና ወቅቱን መሰረት ያደረጉ የአመጋገብ ስርአቶችን ይበልጥ ማስተዋወቅ የሚጠቀሱ ሲሆን ስንዴ፣ ሩዝ፣ በቆሎና ማሽላ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ የአመጋገብ ባህሎች በሃገራት መሪዎችና በሚመለከታቸው አካላት ብሎም በዜጎች ጥረት መስተካከል ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት በፊት ያስጀመረችው የበጋና የቆላ ስንዴ እርሻ እንዲሁም የከተማ ግብርና ስራዎች ከውጭ ሃገራት የሚመጣውን የምግብ ምርትና ለግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም ጎን ለጎን በሃገር ውስጥ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ወደ ውጪ የሚደረገውን ስደት ለመቀነስ ብሎም ገበያውን በማረጋጋት የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማስቀጠልና የምግብ ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው በሚል መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራበት ይገኛል።

በምግብ እህል ራስን መቻል በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው በሚወሰን ሸቀጦች ኢኮኖሚያችን እንዳይጎዳ ያደርጋል። ለከተማ ግብርና ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል። በቦታ ስፋት ሳይወሰኑ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት እራስን መደጎም ያስፈልጋል።   

ጊዜው የፈጠራቸውን መልካም ዕድሎች በአግባቡ መጠቀምም ተገቢ ይሆናል። ይህ እውን የሚሆነው ግን የሚታየውን የገበያ ጉድለት በቅጡ መጠቀም ከተቻለ ብቻ ነው።  በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከውጪ በከምትሸምታቸው እና ዋጋቸው በዓለም አቀፍ ገበያ በሚወሰን ሸቀጦች ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ በርትታ መስራት ይገባታል። የወጪ ንግድ አማራጮቿን በማስፋትም የገበያ አማራጮችን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝነት አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም