ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናትና ኮንፍረንስ በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ተጀመረ

160

አርባ ምንጭ ፤ ግንቦት 5/2014 (ኢዜአ) ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናትና ኮንፍረንስ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ተጀመረ።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው  አውደ ጥናት “ምርምር ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ  የሚካሄድ ስምንተኛው ዙር ሲሆን፤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው።

በግብርናና ባህል ልማት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ፋይዳቸው ላይ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፤ ከ45 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ  ምሁራንና አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 10ኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተጀምሯል።

 “በተግባር ተኮር ምርምርና ፈጠራ ስራ የህብረተሰቡን አቅም መገንባት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ኮንፍረንሱ  የግብርና፣ የጤና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጨምሮ የተለያዩ  የምርምር ውጤቶችና ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል ።

የምርምር ውጤቶቹ እንደ ሀገር የተጀመሩ የለውጥና የዕድገት ጉዞዎች  ዘላቂ በማድረግ ለተሻለ የማህበረሰብ አቅም ግንባታ ሚናቸው የላቀ መሆኑ ተመልክቷል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ኮንፍረንሱ የፌዴራል፤የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ ፤ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።