የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ጥራት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

128

ሐረር፣ ግንቦት 4/2014(ኢዜአ) ልዩ ሐኪሞችን በብዛትና ጥራት በማፍራት የጤና ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሀረላ አብዱላሂ አስታወቁ።

በሐረር ከተማ ''የህክምና ትምህርት ቤቶች ካውንስል በኢትዮጵያ''10ኛ ጉባዔ ዛሬ ተጀምሯል።

ሚኒስትር ዴአታዋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ለሕዝብ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የቅድመና ድህረ ምረቃ ህክምና ተቋማትን ጥራት ለማሻሻል እየተሰራ ነው።

በዚህም ለዘርፉ ቅድመ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብር ዘመኑ የደረሰበትን የህክምና ትምህርት ደረጃ ያማከለ ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ለትምህርት ተቋማት ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

ከ2010 ጀምሮ በ19 ተቋማት ለሚሰጡ 22 የህክምና ስፔሻሊቲ ስልጠና ፕሮግራሞች የተስማማ ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱን ዶክተር ሳህረላ አስረድተዋል።

የህክምና ትምህርት አሰጣጥ ጥራትን በመጨመርና ብቁ ባለሙያዎች በማፍራት ከትምህርት ተቋማቱ የሚወጡ ምሩቃን ችግር ፈቺ  እንዲሆኑ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱን ምሉዕ መሆን ይጠበቅበታል  ብለዋል።

የዘርፉን አገልግሎት ጥራት በማሳደግ  ምሩቃን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በቂ ፋካሊቲ፣ የተግባርና ንድፈ ሀሳብ ልምምድ ቦታዎችን በማደራጀት ጊዜውን በሚመጥን ሥርዓተ ትምህርት እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በጤናው ትምህርት ስልጠና ዘርፍ የረቀቁ የዲጂታል ሲስተሞችን የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ  አመልክተዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስዚዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ መሐመድ ጉባዔው በሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሯቸውን የሚለዋወጡበትና ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው የሚገኙ ተሞክሮዎች ተቋማቱን አንድ ደረጃ ወደፊት እንደሚያሻግሩም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በጉባዔው የመንግሥት የግል የጤና ትምህርት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የሕክምና ትምህርት ቤቶች ካውንስል አመራሮች  ተሳትፈዋል።

''የሕክምና ትምህርት ቤቶች ካውንስል በኢትዮጵያ'' የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ ጥራትን በመጨመር፣ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠትና ብቁ ባለሙያዎች በማፍራት የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳደግ  መቋቋሙን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም