በክልሉ የኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

100

ፍኖተ ሰላም ግንቦት 4/2014(ኢዜአ)”በአማራ ክልል ሁለንተናዊ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚያስችል አካባቢ በመፍጠር ኢኮኖሚውን በተሻለ ማነቃቃት ይገባል” ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ገለፁ።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም በፍኖተ ሰላም እየተካሄደ ይገኛል።

አስተባባሪዋ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በግብርናው ዘርፍ መሪነት ሚናውን እንዲወጣ ያልተቆጠበ ድጋፍና እገዛ እየተደረገ ነው።

ሆኖም የሀገሪቱን የመልማት አቅም በማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎች ኢንቨስትመንትን የሚስብ አካባቢና አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

“በተለይም በግብርናው ዘርፍ ቀደም ሲል በሰራናቸው ስራዎች የማይናቁ ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም፤ ተሞክሯችንን እንደእርሾ በመውሰድ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንትም ውጤት መድገም ይገባናል” ብለዋል።

የግብርናውን ዘርፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ወይዘሮ ዓይናለም፤ ለዘርፉ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮች ፈጥነው ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ ተግባር ተኮር ልማትን በማፋጠን ኢኮኖሚውን በተሻለ ለማነቃቃት ጠንካራ ቅንጅት ፈጥሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደ አባይ ወንዝ መነሻ ያሉ አካባቢዎችን ትኩረት በማድረግ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያመነጭ አካባቢና አቅምን መፍጠር ላይ  እንዲያተኮር ወይዘሮ ዓይናለም አሳስበዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ በበኩላቸው ኢኮኖሚው በሁሉም ዘርፎች መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ወቅቱ የሚጠይቀው አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ዞኑ በግብርና ፣ በቱሪዝምና መሰል የኢንቨስትመንት መስኮች አቅም ያለውና ምቹ አካባቢ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ ባለመልማቱ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በመሆኑም የአሰራር ችግሮችን በመፍታት ባለው የመልማት አቅም ልክ ለምቶ ለኑሮ ውድነት መቀነስና ለኢኮኖሚ እድገት የጎላ ፋይዳ እንዲያበረክት ይሰራል ብለዋል።

”የኢንቨስትመንት የዘርፉን አካላት ትስስር የሚጠይቅ፤ በቅንጅት መሥራትና ችግሮችን በጋራ መፍታት ይገባል” ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንይችል ስለሺ ናቸው።

ለዚህም የኢንቨስትመንት አቅሙንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ድክመቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጥላቸው አስረድተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋትና መዋቅራዊ ለውጥን ማረጋገጥና የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚቻለው በዘርፉ ላሉት ችግሮች የጋራ መፍትሔ ሲቀመጥ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ እየተካሄደ ባለው ውይይት የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ባለሀብቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።