ወጣቶች የሀገርን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

250

ሀዋሳ ግንቦት 04/2014(ኢዜአ) ወጣቶች የሀገርን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ፡፡

"የዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሀገር ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ ለወጣቶች የተዘጋጀ መድረክ ዛሬ በሃዋሳ ተካሂዷል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ኤልያስ እንደገለጹት የሀገር ሰላም መጠበቅ ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዜጎቿን ጥያቄዎች መመለስ የምትችል ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ደግሞ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት መጠበቅና ሀገር አፍራሾችን መታገል እንደሚያስፈልግ በማመላካከት፡፡

''በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ብንሆንም፤ ተስፋ ባላት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው'' ያሉት ኃላፊው፤ ሀገራዊ ለውጥ ያመጣቸውን ዕድሎች እንዳንጠቀም የሚያደርጉ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄ ለማፈላለግ ደግሞ በግልፅ መወያየት ይገባል ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ፀጋ የሆነው ብዝሃነትን እንደ ውበት በመውሰድ ኢትዮጵያዊ ማንነት ማጉላት እንደሚገባም  አቶ አሸናፊ አስገንዝበዋል፡፡

"ጥያቄዎቻችንን መመለስ የምትችል ሃገር ስለምታስፈልገን በአንድነት በመስራት ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጉዞ በወጣቶች እውን ይሆናል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው ወጣቱ የሀገር ተረካቢ ስሜት እንዲኖረው ፅኑ ፍላጎት እንዳለው የገለጹት ኃላፊው፣ በዚያ ስሜት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ በሀገር ግንባታ ሂደት የወጣቱን ሚና የሚገልፅ ሰነድ ያቀረበው የሲዳማ ክልል የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አክሊሉ ዓለሙ ውይይቱ ሀገራዊ አንድነት ለማስጠበቅ ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩ አብዮቶች የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሶ፣ እንደ ሀገር እየገጠሙን ካሉት ተግዳሮቶች ለመውጣት የወጣቱን አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

''በሀገሪቱ በመጣው ለውጥ የክልሉ ወጣቶች ተሳትፎ አመርቂ ነው'' ብሏል።

በሀገርና በሰላም ግንባታ እሴቶች ላይ የመነጋገር ልምድን በማዳበር የወጣቱ ድርሻውን እንዲያሳድግ ጠይቋል፡

በቀጣይም የወጣቶች ሃሳብ የሚንሸራሸሩባቸው የስብዕና ማእከላት እንደሚገነቡና የውይይት መድረኮች እንደሚመቻቹም አስታውቋል፡፡

''ለወጣቶች ምቹ ሁኔታ የማይፈጥር አመራር እንዳይኖር እንደፓርቲ አቋም ይዘናል'' ያሉት ደግሞ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ሾና ናቸው፡፡

ወጣቶች የሃሳብ ትግል በማድረግ ብልሹ አሰራርን እንዲያስቀሩና በፀጥታና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የላቀ ሚናቸውን እንዲጫወቱም ጠይቀዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ ወጣት ኃይለየሱስ ታምራት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን ለማለያየት በተደረገው እንቅስቃሴ ልዩነቶች ላይ እንዲተኮር መደረጉ አስታውሶ፤በወጣቶች ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል ይገባል ብሏል፡፡

''ወጣቶች ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ በማድረግ በሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚጠበቅብን እየሰራን መንግሥትም መስራት ያለበትን ማመላከት አለብን'' ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ወጣት አፈወርቅ ንጋቱ በበኩሉ እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ እንዳንጠቀም የተለያየ አጀንዳ የሚያቀብሉ አካላትን መንገድ መዝጋትና ለወጣቱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቋል፡፡

በመድረኩ በከተማው ከሚገኙ ስምንቱም ክፍለ ከተሞች የተወከሉ ከ400 በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ በሀገር ግንባታ ሂደት የወጣቱን ሚና የሚያሳይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ሰነዱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሊኖራቸው የሚችለውን ተሳትፎ ከመጠቆም ባለፈ፤ በሀገር ግንባታ ሂደት የነበራቸውን ሚና ታረክን በማገናዘብ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም