ህጻን አግቶ ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

208

ጎንደር፤ ግንቦት 4/2014 ( ኢዜአ ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ታዳጊ ህጻንን በማገት ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው በጭልጋ ወረዳ የቤዛሆ መቀነት  ቀበሌ ነዋሪ በሆነው አበበ ዳኘው ላይ መሆኑን የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመው በወረዳው  የአይከል ከተማ ነዋሪ የሆነውን የ15 ዓመት ዕድሜ ያለውን ታዳጊ ህጻን ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤቱ አፍኖ በመውሰድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለህጻኑ ወላጆች ስልክ በመደወል 100 ሺህ ብር ከፍለው ልጃቸውን እንዲወስዱ ብሩን ካልከፈሉ ግን ህጻኑን እንደሚገድለው ሲዝት እንደነበር  ገልጸዋል።

በዛተውም መሰራት ህጻኑን በወረዳው ፋይና ገብ ተብሎ በሚጠራው ገደል ውስጥ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉን በሰውና በህክምና ማስረጃ መረጋገጡን ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ክስ ከሰማ በኋላ ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠይቅ ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል፡፡

ተከሳሽ በአቃቢ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ  ማስተባበል ባለመቻሉ  በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ- ሥርዓት የህግ ቁጥር 149/1/ መሰረት ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ግለሰቡ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔው እንዳስተላለፈበት  የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ገልጸዋል።