በመዲናዋ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ከደረቅ ቆሻሻ ሽያጭ 113 ሚሊዮን ብር ገቢ አገኙ

130

ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ) በመዲናዋ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከደረቅ ቆሻሻ ሽያጭ 113 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው መደበኛ ቆሻሻን ከመለየትና ከማስወገድ ሥራ በተጨማሪ የንቅናቄ ሥራዎችን እየተገበረ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በማህበራት የተደራጁ ወጣቶች ሃይላንዶችን፣ ላስቲኮችን፣ ወረቀቶችንና መሰል ተረፈ-ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ማህበራቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኙ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ የመዲናዋ ወጣቶችም በዚሁ የሥራ ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ አካባቢዎችንና ብሎኮችን ሞዴል የማድረግና እውቅና የመስጠት ስራ መከናወኑን አስታውሰዋል።

የንቅናቄ ሥራውን የሚያግዙ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰራተኞችን በመቅጠር ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ትምህርት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተጀመረው የጽዳት ንቅናቄ በተለይ ኅብረተሰቡ ስለ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የጽዳት ንቅናቄ መቀጠሉን ገልጸው፤ ዘመቻው ቆሻሻን ከማንሳት ባሻገር ስለቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

በመዲናዋ የጽዳትና ውበት ሥራ ዘላቂ ሆኖ በቆሻሻ ምክንያት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቀነስ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።