የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርት የሚደብቁ ህገወጦችን ለመቆጣጠር የንግዱ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

121

ሀዋሳ፣ ግንቦት 04 ቀን 2014 ( ኢዜአ) ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርት የሚደብቁ ህገወጦችን በመቆጣጠር ለማስተካከል ለሚወሰደው እርምጃ የንግዱ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ።

“የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ ለንግዱ ማህበረሰብ የተዘጋጀ  የውይይት መድረክ ዛሬ  በሀዋሳ ከተማ  ተካሂዷል።

በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እና ለውይይት መነሻ የሆነውን ፅሁፍ ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ በላይነሽ ገዳ እንዳሉት፤ ነጋዴው ማህበረሰብና ባለሀበቱ ሰርቶ ያፈራውን ሀብት ማሳደግ የሚችለው ሠላም ሲኖር ነው።

ሠላም ሲታወክ የሰመረ የንግድ ሥርዓት እንቅሰቃሴ ሊኖር አይችሉም ያሉት ኃላፊዋ፤ ከዚህ አንፃር የንግዱ ማህበረሰብ  የሀገሪቱን  ሰላም ማስፈን ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ እና የንግድ ህጋዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እና ምርት የሚደብቁ ህገወጦችን በመቆጣጠር ለማስተካከል ለሚወሰደው እርምጃ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል ።

ህገ ወጥ አሰራር እንዲስፋፋ የሚፈልጉ በተለይ የሲሚንቶ አስመጪ ነጋዴዎች ድርጅታቸውን ዘግተው በመጥፋት የምርት እጥረት እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከሲሚንቶ ፋብሪካ አንዱን ኩንታል በ540 እና 560 ብር ሂሳብ ተረክበው ሲያበቁ በተጋነነ ዋጋ በ1 ሺህ 300 ብር ሂሳብ ሲሸጡ እንደተደረሰባቸው ጠቁመዋል።

እንዲሁም በከተማዋ የምግብ ዘይት እጥረት እንዲከሰት እና  በዋጋ ንረት ህብረተሰቡ እንዲማረር ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ለሲዳማ ክልል ህዝብ የሚበቃ ዘይት ተከማችቶ መገኘቱን ነው ያስታውቁት።

በንግድ ስርዓቱ በኩል የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ተፈተው የነጋዴው ማህበረሰብ በተረጋጋ እና ህግን አክብሮ እንዲሰራ በማድረግ በኩል የከተማ አስተዳደሩ አበክሮ  ይሰራል ብለዋል ሃላፊዋ።

የንግዱ ማህበረሰብ ከግለኝነት አስተሳሰበ በፀዳ መልኩ ለሀገር ሠላም ግንባታና ለዜጎች ብልጽግና መረጋገጥ በቁርጠኝነት የድርሻውን እንዲወጣም  ጠይቀዋል።

የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ኤልያስ በበኩላቸው፤ መድረኩ ዜጎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጠራ እና የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሀገራችን እየተስተዋሉ ያለው ሠላም እጦት መነሻ ከሆኑ  አክራርነትና  ጽንፈኝነት ባልተናነሰ መልኩ  የኑሮ ውድነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፤   የንግዱ ማህበረሰብ ህግ እና ሥርዓቱን ባከበረና በመተሳሰብ መንፈስ  በመስራት ሀገሪቱን ለማሻገር በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚናውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ፍሬው በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ የከተማዋን ኢኮኖሚ እንዲያድግ  በአካባቢው የልማት እንዲፋጠን  የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ገና ለገና ዋጋ ይጨምራል በማለት እቃ የመያዝና የመሰወር ተግባር በአንዳንድ ነጋዴ ዘንድ እንደሚታይ ጠቁመው፤ አሁን ካለንበት ሁኔታ አንጻር እራሳችንን በመፈተሽ ይህንን ጊዜ በመተጋገዝ ልናሳልፈው  ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የሀዋሳ የብርቂቱ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሰብስቤ ገብሩ በበኩሉ፤ መድረኩ በችግሮቻቸው  ዙሪያ በጋራ በመምክር  ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጿል።

አሁን ላይ የሀገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች  ስራ አጥ ወጣቶችን መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸው መንግሥት ጎልቶ የሚታየውን የስራ አጥ ችግር  ማቃለል እንዳለበት አመልክቷል።